ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሯቸውን ህዝባዊ ለውጦች በሙያችን ለመደገፍ ዝግጁ ነን- አርቲስቶች

2878

አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010 ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሯቸውን አገራዊና  ህዝባዊ ለውጦች በሙያቸው ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አርቲስቶች ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ላለፉት ሶስት ወራት ያመጧቸውን ለውጦች ተከትሎ በዛሬው ዕለት በመስቀል አደባባይ የተካሄደውን የመደመር የድጋፍ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን ለውጡ የአገሪቱን መፃኢ እድል ወደተሻለ ደረጃ የሚወስድ ነው ብለዋል።

በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን እንዲሁም ኢትዮጵያዊ አንድነትን ከማጠናከር አኳያ ትልቅ መነቃቃት መፈጠሩንና ይህም የህዝቡ ቀዳሚ ፍላጎት መሆኑን ገልፀዋል።

አሁን የተጀመረው ዴሞክራሲያዊ መነቃቃት ለአገሪቷ ቀጣይ እድል መንገድ የሚከፍትና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መሆኑንም ገልፀዋል።

በተለይም ሰላምን ከማስፈን፣ ጥላቻን ከማስወገድ፣ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን ከማጠናከር አኳያ የተጀመረው ስራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ማህበረሰብ በጋራ ሊያምንበትና ሊሰራበት የሚገባ ነው ብለዋል።

አርት ማለት የህብረተሰቡን አኗኗርና መልካም ባህል የሚያሳድግ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ሰላምን፣ አንድነትንና አብሮነትን ለማጎልበት ትልቅ ሚና ያለው ሙያ መሆኑን የገለፁት አርቲስቶቹ “እኛም በሙያችን ለውጡን ለማስቀጠል እንሰራለን” ሲሉ ቃል ገብተዋል።