የሰብዓዊ መብት ጥበቃና የሚዲያ ሚና

140

በቁምልኝ አያሌው (ኢዜአ)

ኢትዮጵያ ቀደምትና የሃገረ መንግስት መስተዳደር ባለቤት መሆኗን የተለያዩ የታሪክ መዛግብቶች ያስረዳሉ። አገሪቷ ለረጅም ዘመን በተለያዩ መሪዎችና ህገ-ስርዓትም ጭምር ስትመራ ብሎም ስትተዳደር ቆይታለች፡፡በነዚሁ የመንግስት አስተዳደርና ህገትግበራ ስርዓት ሂደት ውስጥም መሪዎች ለህዝባቸው ይሆናሉ ያሏቸውን የየራሳቸው ህግጋቶችን በማውጣት አንዱ የአንዱን የህግ አስተዳደር ስርዓት እያሻሻሉ አለፍ ሲልም እያጠፉ ይኸው እዚህ ደርስናል። ላለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት ገደማ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው ገዢው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በብሔርና ቋንቋ ላይ የተመሰረተ የፌደራሊዝም አስተዳደር ይከተላል።

ለዚሁ ብሄርና ቋንቋን መሰረት ላደረገው የአስተዳደር ስርዓት መዋቅርም ይበጃል ተብሎ የተደነገገ ህገ መንግስት ሥራ ላይ እየዋለ ይገኛል። ህገ መንግስቱ በአስራ አንድ ምዕራፎች፣ በ106 አንቅፆች እና በርከት ባሉ ንዑስ አንቀፆች ተከፋፍሎ እናገኘዋለን።

በህገ መንግስቱ ከተካተቱት ድንጋጌዎች መካከልም በዋናነት የዜጎች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት በተሟላ ሁኔታ እንዲረጋገጥ በሚል ሰፊ ሽፋን ተሰጥቷቸው ይገኛል፡፡  የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ “አመለካከትን እና ሀሳብን በነፃነት የመያዝ እና የመግለፅ መብትን” በደነገገበት አንቀፅ 29 ላይ በሰባት ንዑሳን የተዘረዘሩ ወሳኝ ጉዳዮችን ይዟል። እነዚህም ማንኛውም ሰው የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ እንደሚችል፣ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዳለው፣ የፕሬስና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የሥነ-ጥበብ የፈጠራ ነፃነት መረጋገጡን ብሎም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሀሳቦች እና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነት እና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ እንደሚደረግለት የሚገልፁ መብቶች ናቸው።

ከዚህ አኳያም በህገ-መንግስቱ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰብዓዊ መብት ስንመለከት ሰው፤ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ እኩልና የሰብዓዊ ፍጡራን መብት ባለቤት መሆኑን ይደነግጋል፡፡ የዴሞክራሲያዊ መብትን  በተመለከተ ደግሞ የመፃፍ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና፣ የመናገር ነፃነትና መብትን አጎናፅፏል፡፡

ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ (UDHR-1948) ካስቀመጠው ትርጓሜ ስንነሳ የሰብዓዊ መብት ማለት ፆታን፣ ዘርን፣ ዜግነትን፣ ሃይማኖትን፣ ጎሳን ቋንቋን እንዲሁም ሌላ ሁኔታን ጨምሮ የሰው ልጅ ሁሉ ሊያገኛቸው የሚችሉ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶችን ያለ ምንም ገደብ ያካተተ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ በሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ላይ ጥናት ያደረገ ኤን በሄበሄ የተሰኘ የዘርፉ ምሁር "የሰብዓዊ መብቶች እና ነፃነቶች በዓለም ላይ ላሉት እያንዳንዱ የሰው ልጆች ሁሉ ከውልደት እስከ ሞት ድረስ ባለው የህይወት ዑደት ላይ  በማንም አካል ሊወሰዱና ሊገፈፉ የማይችሉ ናቸው" ሲሉ ያስረዳሉ።

እነዚህ የሰው ልጆች ሁሉ የሆኑት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች መንፀባረቅ የጀመሩት በዓለም ዓቀፉ ጦርነት ወቅት የጀርመኑ መሪ ሂትለር በአይሁዳዊያን ዜጎች ላይ ባደረሰው ጭካኔ ከተሞላበት የዘር ማጥፋትና ጭፍጨፋ ተግባር በኋላ እንደሆነ የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

እኒህ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ እና በባህላዊ ጉዳዮች ውስጥ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መጠበቅ እንዲችሉ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲያቀነቅኑ እንደነበርም ይገለፃል። መገናኛ ብዙሃን ደግሞ እንደ አንድ ማህበራዊ ተቋም እነዚህ መሰረታዊ የሆኑ የሰው ልጆች መብቶችና ነፃነቶችን ለመጠበቅ፣ ለማክበር፣ ለማስከበር ብሎም ለማስተዋወቅና ግንዛቤ ለማስጨበጥ የጎላ ሚና አላቸው።

በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን እንደሚያስረዱት ሚዲያ ማለት ሃሳብ በነፃነት እንዲንሸራሸር የሚያደርግ የተግባቦት መሳሪያ ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን ማለት በእያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚፈጠሩና የሚከወኑ የዕለት ከዕለት ተግባራት ውስጥ አስተማሪ፣ ገንቢ፣ እውቀት ሰጪ በተቃራኒውም ደግሞ አስከፊ፣ አሳዛኝና መጥፎ የሆኑ ጉዳዮችን በዜና፣ በመዝናኛ፣ በፊልም፣ በትያትር እና በመሳሰሉ የአሰራር ዘዴዎች  መልክ የማሳወቅ ስራ እንደሆነም ይገለፃል።

ጋዜጠኞች ቀደምት ከሆኑት የመገናኛ ብዙሃን እንደ ራዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና የህትመት ውጤቶች በተጨማሪ በአዲስ መልክ በበየነ መረብ አማካኝነት በስልክና በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛዎች ለሰፊው የህብረተሰብ ክፍል መረጃን ለማድረስ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። መገናኛ ብዙሃን ከትርጓሜው እንደምንረዳው ለህብረተሰቡ ባለው የግንኙነት መስመር አማካኝነት የሰው ልጆችን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ለማስጠበቅ የተለያዩ ዜና እና ዜና ነክ ስራዎችን አካቶ መረጃ በማድረስ  የማይተካ ሚና ይጫወታል። ይህ ብቻም ሳይሆን ሚዲያ በሃገራችን በሚስተዋሉ መሰረታዊ የሰው ልጆች መብትና ነፃነት ላይ በሚስተዋሉ የአመለካከት ግድፈቶችንና ችግሮችን በማባባስ፣ በመተንተን፣ ቅርፅ በማስያዝ ብሎም በማበረታታት ረገድ የየራሳቸው የሆነ አሉታዊና አዎንታዊ ዝንባሌ አላቸው።

የመገናኛ ብዙሃን ሚናን በሚመለከትም ጀስፐር ስትሮምባክ የተሰኘ ፀሃፊ "ሚዲያ በህዝቡ ውስጥ የሚያከናውነው የዕለት ተዕለት ተግባር አለው" ሲል ተግባራቸውን ያብራራል፡፡ በዚህ ተግባራቸውም የህዝቡን ሁለንተናዊ እንቅስቀሴዎችን በመከታተል ለተደራሲያን ያቀርባሉ።  የመገናኛ ብዙሃን ከሰብዓዊ መብትና ነፃነት አኳያም ግንዛቤ በማሳደግ፣ የወጡ ፖሊሲና አዋጆችን በማስተዋወቅ እና በማስተማር ብሎም የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ተፅዕኖ ሲኖርም በማጋለጥና ድምፅ በመስጠት፣ የተጎጂዎችን ችግር በይፋ ተጋፍጦ በማውጣትና በማሳወቅ ለሚመለከታቸው አካላትና ለሰፊው የህብረተሰብ ክፍል መረጃ እንዲደርሳቸውም ጭምር የማድረግ አቅም አላቸው።

የመገናኛ ብዙሃን ካላቸው ሚና አንፃር በዓለም ዓቀፍ፣ በአፍሪካ ብሎም በሃገራችን ደረጃ የሰብዓዊ መብት ጥበቃን በሚመለከት የተፈጠሩ ክስተቶችን የማስፋት፣ የማስተጋባትና የማሰራጨት ሰፊ አቅም አላቸው። ከሰብዓዊ መብትና ነፃነት ጥበቃ ጋር በተያያዘ ከተከሰቱት ሁነቶች አኳያም የዜና ሽፋን በመስጠት፣ ትንታኔ በመስራት፣ የውይይት መድረክ በመፍጠር እና በማስተማር ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫዎቱት ሁሉ በአዘጋገብና በአሰራር ሂደታቸው የሚሰጧቸው የይዘት አዝማሚያ ላይ ከፍተኛ የሆነ  አሉታዊ ተፅዕኖም ሊያሳድሩ እንደሚችሉ መታወቅ አለበት።

ይህ የሚሆነውም እያንዳንዱ መገናኛ ብዙሃን ካለው የፖለቲካ ኢኮኖሚ የሃይል ግንኙነት ፍላጎት አንፃር የሚዲያው የገቢ መንጭ ምንድን ነው? የጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ-ምግባር በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ብሎም መረጃን ለአድማጭ ተመልካቾች እንዴት በተሻለ መንገድ ለማሰራጨት እንችላልን? በሚሉት ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ መሆኑንም መረዳት ይጠይቃል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን የመገናኛ ብዙሃን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ እና ማስተዋወቅን በሚመለከት ግንዛቤን በማሳደግ፣ በማስተማር ብሎም በማነፅ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው የሚታበይ ጉዳይ አይደለም።

ሚዲያ የሰብዓዊ መብትን በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ በማዘጋጀት፣ ለዜጎች መረጃን ለማድረስ፣ በሬዲዮ ቶክ-ሾው መልክ በማቅረብ እንዳንዱ የህብረተስብ ክፍል መብቱን አክብሮ በማስከበር የሰብዓዊ መብት ጉዳይም ትልቅ አጀንዳ እንዲሆን የሚያስችል መረጃን የማስተላለፊያ ዘዴ መሆን ይጠበቅበታል። በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ዙሪያ ስላሉ እሴቶች የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ዋናው ጉዳይ ሲሆን፤ በዘርፉ ግንዛቤው የጎለበተ፣ ያወቀና የተገነዘበ ማህበረሰብ መፍጠር ደግሞ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጡ መብቶችና ነፃነቶችን አክብሮ ለማስከበር ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።

ሚዲያ ድምፅ አልባ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ በመሆን በመንግስትና በአጠቃላይ አድማጭ ተመልካቹ መካከል ቋሚ የግንኙነት መስመር በመገንባት ለሰብዓዊ መብት መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበርክታል። ከዚህ በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና አካላት የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ እንዲናገሩ እና የደረሰባቸውን በደል ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ እንዲችሉ መድረክንም ያመቻቻል፤ ያወያያል።

በዚህ ሂደትም ሚዲያ የሰብዓዊ መብትን ለማስጠበቅና የሚፈጠሩ ጥሰቶችን በስልጣን ላይ ያሉ አካላትም ጉዳዩን በመመርመር አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡበት ብሎም ጉዳዩም  የህዝብ አጀንዳ እንዲሆን ለማስቻል ያግዛል። እንደምሳሌ ብንመለከት እንኳን እ.አ.አ. በ2011 በአረብ አብዮት ሲናጡ ከነበሩ ሃገራት መካከል በቱኒዚያ የነበረውን የአምባገነናዊ መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተለያዩ ሚዲያዎች የዜጎች መብት እንዲጠበቅ ሰፊ ሽፋን በመስጠት ሲያስተጋቡ እንደነበር የቅርብ ክስተት ነው።

በመሆኑም ሚዲያ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጡ መብትና ነፃነቶች እንዲከበሩ፣ ሰፊ ትኩረትና ሽፋን እንዲያገኙ ትልቅ ሃይል መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተለይ በቱኒዚያ ተካሂዶ ከነበረው የአረብ አብዮት ማግስት ለመረዳት የቻልነው ሚዲያ የዜጎች ሁለንተናዊ መብት እንዲከበር፣ የህግ-የበላይነት እንዲሰፍን፣ መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን ነው። ስለሆነም ሚዲያ ድምፅ ለተነፈጉ ዜጎች ብሎም የህብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ በመሆን  የሰብዓዊ መብቱ እንዲጠበቅ ወሳኝ ሚና መጫወት እንደሚችል መታወቅ የሚገባው ጉዳይ ነው። አለን ቶምሰን የተባለ በመገናኛ ብዙሃንና ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ የተለያዩ ስራዎችን ያከናወነው ምሁር እንደሚለውም "መገናኛ ብዙሃን የህዝብ ተሳትፎ መድረክ መሆናቸውን" ይገልፃሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን በፖሊሲ አወጣጥ ውስጥ የህብረተሰብ ተሳትፎ እንዲኖር ለማንቃት ያግዛሉ ይላሉ።

በተለይም አሁን ባለንበት የ21ኛው ከፍለ ዘመን እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዌብ-ሳይት፣ ኦላይን ቲቪ እና የመሳሰሉት ዓይነት አዲስ የበይነ መረብ መገናኛ አውታሮች መምጣትና መብዛት ዜጎች ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው መብታቸውን ለማስከበር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳባቸውን ማንሸራሸር እንዲችሉ እድል ከፍቷል፡፡ ምንም እንኳን ላልተገባ አላማ እየዋለ ቢገኝም ህዝብ ከህዝብ በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ ቢሰራበት አዲሱ የማህበራዊ ሚዲያ ሰፊው የህብረተሰብ ክፍል ስለሚጠቀመው በስፋት ተደራሽ በማድረግ በሰብዓዊ መብት አያያዝና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።

"ሚዲያ በሰዎች፣ በመንግስትና በሲቪክ ድርጅቶች መካካል ያለ ድልድይ በመሆኑ፤ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጊዜ ወሳኝ የሆነ ሚና ይጫወታል" ሲሉ የሚዲያን ጠቀሜታ የሚያስረዱት ደግሞ ሰብዓዊ መብትና ሚዲያ ጥበቃ ባለሙያው ሞሃመድ ራዛብ ሀቢብ  ናቸው፡፡ መገናኛ ብዙሃን መንግስት በሰብዓዊ መብትና ነፃነቶች ዙሪያ ያከናወናቸውን ተግባራቶች የመመርመርና ሂደቱንም ተከታትሎ የማስረዳት ግዴታ እንዳለበትም ሊታወቅ ይገባል።

ይህኑ ሃሳብ ለማጠናከርም ማክ-ቋይል የተባሉ የዘርፉ ፀሃፊ "የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መኖር አለመኖራቸውን ሚዲያዎች በየጊዜው የመከታተል ግዴታ እንዳለባቸው" ያሳስባሉ።

እናም ሚዲያዎች በዓለም ዓቀፍ፣ በአፍሪካ ብሎም በሃገራችን ደረጃ የሰብአዊ መብቶችን አክብሮ በማስከበር፣ ግንዛቤን በማሳደግና በማስተማር፣ ጥሰቶችን በማጋለጥና ሽፋን በመስጠት ትልቅ የማህበራዊ መወያያ አጀንዳ እንዲሆኑ በማድረግ ወሳኝ ሚና መጫዎት ይኖርባቸዋል፡፡ በስራና አሰራር መስተጋብራቸውም ቢሆን የሰብዓዊ መብትና ሚዲያ ነፃነት ሊነጣጠሉ ከቶ አይቻላቸውም፡፡ አሁን ባለንበት ዘመናዊ አለምም ሰብዓዊ መብትን በሚመለከት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ጉዳዮች በሚኖሩበት ወቅት ድምፅ ሰጥቶ ለማስተጋባት ሚዲያ ቁልፍ ስፍራ ይሰጠዋል።

የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ና ትኩረት እንዲሰጠው የመገናኛ ብዙሃን ገንቢ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፤ መጫወትም ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም በሚዲያ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብትን ለማስጠበቅ የሚያድርጉት እንቅስቃሴ እንዲበረታታና ሌሎች አካላትም ተመሳሳይ ስራ እንዲሰሩ ከተፈለገ የሚፈለገውን የሰው ሃይል በመደገፍና በማሰማራት  የሚዲያ ነፃነት መስጠት ከመንግስት ይጠበቃል።

በሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን የግልና የመንግስት ተብሎ መከፈል ያለና የተለመደ ቢሆንም አሁን አሁን የብሄርና የተለያዩ ቡድኖች መገናኛ ብዙሃን እያቆጠቆጠ ነው፡፡ አንድን ብሄር እወክላለሁ ብሎ የሚቋቋም መገናኛ ብዙሃን በአግባቡና ዲሞክራሲዊ በሆነ መንገድ ቢወክል መልካም የነበረ ቢሆንም፤ እውነታው ከዚህ የራቀ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በሀገራችን የሚገኙ በመገናኛ ብዙሃንም  አንዱን ለመጥቀም ሌላውን ማጣጣልና መጉዳት እየተስተዋለ ነው፡፡ ጎሰኛ መገናኛ ብዙሃን በመርህ የሚመራው ጋዜጠኝነት ከአቀንቃኝነት ጋር መቀላቀሉም አዲስ ሁነት ሆኖ የዘጎችን መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ለማስከበር ያለው ፋይዳ እምብዛም ሆኗል።

የሚገርመው ደግሞ መንግስት በዚህ ወቅት የዴሞክራሲ ምህዳርን ከማስፋት ጎን ለጎን መገናኛ ብዙሃን ገለልተኛ ሆነው ከማንም መንግስታዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ቢደረግም አይደለም የሰብአዊ መብት ከለላና ጥብቃ ላይ ሊሰሩ የሆነውንና ያልሆነውን በማሰራጨት ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ የሚያቃቅር ተግባር ውስጥ የገቡ መገናኛ ብዙሃን እንዳሉ የብሮድካስት ባለስልጣን በተለያየ ጊዜያት የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ያስረዳሉ። በመሆኑም መንግስትና ባለድርሻ አካላት እነዚህን አደራጃጀቶች በመፈተሽ የዜጎችን ሰብአዊ መብት እንዲከበር መገናኛ ብዙሃን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንዲሰሩ ማድረግ ይኖርበታል።

በጥቅሉ ሚዲያ የዜጎችን መብትና ግዴታን ለህዝብ ለማሳወቅ፣ ድምፅ ሆኖ ለማስተጋባት፣ ለማስተማር ብሎም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመጠቆም እና የሰው ልጆች መብት ሁሉ እንዲጠበቅ ለማድረግ የሚያስችል ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ በመሆኑም ሀገርን የሚያስተዳድረው መንግስትም የዜጎች መብትና ነፃነት መረጃ የማግኘት ጉዳይ በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የተሟላ የሰው ሃይል እንዲኖረው በማድረግ ቋሚነት ያለውና ከሚሄደው ጋር ወገንተኛ ያልሆነ ተቋም መገንባት ይጠበቅበታል፡፡ የሃገር አስተዳዳሪ መንግስታት ቢቀያየሩም ዜጎች ግን በአንዲት ሃገር ውስጥ ይኖራሉና፤ ለሰው ልጅ ተፈጥሯዊ መብቶች ሰፊ የሚዲያ አስተምህሮ ሽፋን በመስጠት እና ግንዛቤ በማሳደግ እንደሃገር ሁሉም ዜጋ ተከባብሮ፣ ተባብሮ፣ ተቻችሎና እኩል ተጠቃሚ ሆኖ ሚኖርባትን  ኢትዮጵያ መፍጠር  ለነገ የማይባል ተግባር ነው። ሰላም!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም