አራተኛው ዙር የህዝብና የቤት ቆጠራ ሙሉ በሙሉ በታብሌት ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ 30 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል

75
አዲስ አበባ  ሰኔ 16/2010 አራተኛው ዙር የህዝብና ቤት ቆጠራ ካለፉት ጊዜያቶች በተለየ መልኩ በታብሌት ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ለማድረግ 30 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ። የህዝብና የቤት ቆጠራ በየአስር አመቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል። በአሁኑ ወቅት አራተኛውን ዙር የህዝብና የቤት ቆጠራ ለማካሄድ አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን በማካሄድ ላይ መሆኑን ኤጀንሲው ጠቁሟል። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አበራ  እንደገለጹት፤ በህዝብና የቤት ቆጠራ የሚሰበሰቡ መረጃዎች ለአገር እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በቆጠራው የሚሰበሰበው መረጃ በትምህርት፣ በጤና፣ በስራ-ሁኔታ፣ በስርዓተ-ጾታና በተለያዩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እቅድና ፖሊሲ ዝግጅት ወቅት ላቅ ያለ እገዛ ያደርጋል። አራተኛው ዙር አገር አቀፍ የህዝብና የቤት ቆጠራ ስራ በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም አገሪቱ ላይ በነበረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋ ባሳለፉት ውሳኔ ቆጠራው በ2011  እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውሰዋል። በመሆኑም ለህዝብና የቤት ቆጠራ ስራው ውጤታማነት አዲስ የታብሌት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቆጠራውን ለማከናወን በአጠቃላይ 180ሺህ ታብሌቶች የተዘጋጁ ሲሆን ለዚህም 30 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን ገልጸዋል። በገጠር እንዲሁም ሩቅና አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች ላይ የሃይል አቅርቦት እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት በቆጠራው ላይ የመቆራረጥ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በፀሐይ ኃይል የሚሞሉ ቁሳቁሶች (ሶላር ፓወር ባንኮች) መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። በዚህም የህዝብ ቆጠራ ኮሚሽን በማቋቋም የቆጠራ ቦታ ካርታ በማዘጋጀት፣ መጠይቆችና መመሪያዎችን በማዘጋጀትና በሌሎችም ተግባራት ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። መረጃ በአግባቡ ለመሰብሰብ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጁ መጠይቆች በእንግሊዝኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግረኛ፣ አፋርኛና ሶማልኛ በአጠቃላይ በአምስት ቋንቋዎች ተተርጉመው መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል። በመሆኑም እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል የህዝብና የቤት ቆጠራ በሚካሄድበት ወቅት ትክክለኛ መረጃዎችን በፈቃደኝነት ለቆጣሪዎች ወይም ለመረጃ ሰብሳቢዎች በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም