በአማራ ክልል ፍትሃዊ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነት ችግር ለመፍታት ውስንነት እንዳለ ተገለጸ

92

 ኢዜአ ታህሳስ 21/2012 የአማራ ክልልን ፍትሃዊ የመሰረተ- ልማት ተጠቃሚነት ችግር ለመፍታት የተደረገው ጥረት ውስንነት እንዳለበት የክልሉ የመሰረተ ልማት አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ገለጹ። ኮሚቴው  በክልሉ እየተከናወኑ ባሉ የመሰረተ ልማት ጉዳዮች ላይ በባህር ዳር ከተማ መክሯል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የመሰረተ ልማት አማካሪ የኮሚቴው አባል  አቶ ደሳለኝ አስራደ እንደገለጹት   ባለፉት ዓመታት በሚካሄዱ  የመሰረተ ልማት ክልሉ ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል።

በሚካሄዱ የመንገድ፣ የቴሌ፣ የኤሌክትሪክ መብራትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግር እንዳለ ህዝቡ  በተደጋጋሚ በማንሳቱ አመራሩ ጥያቄውን ተቀብሎ ለማስተካከል ሙከራ ማድረጉን ተናግረዋል።

የሚገነቡት የመሰረተ ልማቶችም አቅም በሌላቸው የስራ ተቋራጮች ስለሚሰጡ ከተደራሽነት ውስንነት ባሻገር የጥራት ችግርም መከሰቱን አመልክተዋል።

በተካሄደው  ጥናት መሰረት ፍትሃዊነት ቢኖር ባለፉት  ዓመታት  በኃይል ተደራሽነት ብቻ  ክልሉ እንደ ሀገር 37 የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ  ሰብስቴሽን ይኖሩት እንደነበር ጠቅሰዋል።

"በክልሉ አሁን ላይ 26  ስብስቴሽኖች እንዳሉትና ከነዚህም   ሰባቱ ብቻ ናቸው በሙሉ አቅማቸው  አገልግሎት መስጠት የሚችሉት" ብለዋል።

በሌሎች የመሰረተ ልማት ዘርፎችም ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ገልጸው  ከሚመለከተው አካል ጋር ተወያይቶ ችግሩ እንዲፈታ በማድረግ በኩልም ውስንነት መኖሩን ጠቁመዋል።

በየደረጃው የሚገኝ አመራር ብሶት ማውራት ብቻ ሳይሆን  ፈጥኖ ችግሩ  በሚፈታበት ጉዳይ ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

 "እንደ ክልል የነበረውን ፍትሃዊ  የመሰረተ ልማት ችግር  በመረጃና በማስረጃ  ተደግፎ  በጥናት ተረጋግጧል" ያሉት ደግሞ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል ናቸው።

ችግሩን ለመፍታት ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችም በተለያዩ ምክንያቶች እየተጓተቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ተጨማሪ የመሰረተ ልማት አውታሮች  መጠየቁ እንዳለ ሆኖ  እየተገነቡ ያሉት የመንገድና  ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዳይደናቀፉ  በየደረጃው ያለ አመራር ትኩረት ስጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

 የክልሉ ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛት አብዩ በበኩላቸው ።"ሁል ጊዜ  ስለ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግር ብቻ  ሳይሆን ችግሩን መፍታት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ማተኮር ይገባል" ብለዋል።

ከቀበሌ እስከ ክልል ያለው አመራር የሚስተዋሉ ችግሮችን ማውራት እንጂ እንዴት ይፈቱ ብሎ የመፍትሄ አካል ከመሆን አንጻር  ሰፊ ክፍተት እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

በፌዴራልና በክልሉ እንዲሰሩ አቅጣጫ ተስጥቶባቸው የሚገኙ በርካታ ፕሮጀክቶችን ጥራት በመከታተልና ወሰንን በማስከበር  በኩል የሚስተዋለውን ክፍተት ለማስተካከል ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል።

"አመራሩ  በራሱ የሚስተዋሉ ችግሮችንም መፍታትና ለፌዴራል መቅረብ ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ተግባብቶ በጋራ መስራት አለበት " ብለዋል።

የክልሉ  የመሰረተ ልማት  አስተባባሪ ኮሚቴ የዘርፉን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርና ለመከታተል ቀደም ብሎ  የተቋቋመ ሲሆን  የሚመለከታቸው የዘርፉ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶችን በአባልነት የሚገኙበት ነው።

በአማራ ክልል ከሚገኙ ሶስት ሺህ 945 ቀበሌዎች መካከል አንድ ሺህ 699 ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ  አገልግሎት ተደራሽ መሆናቸውን  አስተባባሪ ኮሚቴው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም