በክልሉ የባህል ምሽት ቤቶች በአንድነትና በአብሮ መኖር ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ጥረት እየተደረገ ነው

90
ኢዜአ ታህሳስ 21 / 2012  በአማራ ክልል በዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች የሚገኙ የባህል ምሽት ቤቶች በአንድነት እና በአብሮ መኖር ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ እንድሪስ አብዱ ለኢዜአ እንደተናገሩት ባህላዊ የምሽት ቤቶች የክልሉን ታሪክ፣ ባህልና ወግ በስፋት በማስተዋወቅና የቱሪስቶችን ቆይታ በማራዘም በኩል ፋይዳቸው የጎላ ነው፡፡ ምሽት ቤቶቹ የሀገርን ገጽታ በመገንባትና የእንግዳ ተቀባይ ባህልን የሚያጎሉ የኪነጥበብ ስራዎችን በየምሽቱ በማቅረብ ቱሪስቶችንና እንግዶችን በስፋት በማዝናናት እንደሚታወቁም አመልክተዋል፡፡ በተቃራኒው በአንዳንድ ምሽት ቤቶች በአሁኑ ወቅት የክልሉን ባህል፣ ታሪክና ማንነት በአግባቡ ከመግለጽ ይልቅ ለግጭት የሚያነሳሱ፣ አንድነትን የሚሸረሽሩና የሚከፋፍሉ ሃሳቦች እየተንጸባረቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "ቢሮው ችግሩን ለማስተካካል በየደረጃው ካለው የመንግስት መዋቅር ጋር በመቀናጀት ችግሩ የሚስተዋልባቸው የባህል ምሽት ቤቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ቀደም ሲል ምክርና ውይይት አካሂዷል" ብለዋል አቶ እንድሪስ፡፡ ከምክር ባለፈም ህጋዊነትን ተከትለው እንዲሰሩና በዘርፉ የወጡ ህጎችን ለማስከበር የማስጠንቀቂያና የማሸግ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱንም ነው ምክትል ቢሮ ኃላፊው የገለጹት፡፡ እንደኃላፊው ገለጻ የባህል ምሽት ቤቶቹ የግጭት ነጋሪቶች የሚጎሰሙባቸው ከመሆን ተላቀው የአንድነትና የፍቅር መገለጫና የኪነጥበብ መልካም እሴቶች መገንቢያ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡ በቀጣይም በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች በምሽት ቤቶች ለሚሰሩ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና የተቋማቱ ባለቤቶች  ተጨማሪ ስልጠናዎችና የምክክር መድረኮች እንደሚዘጋጁም አቶ እንድሪስ አመልክተዋል፡፡ በአንዳንድ ምሽት ቤቶች የሚስተዋለውን የድምጽ ብክለትና የስነ-ምግባር መጓደል በመቆጣጠር ህግና ስርአቱን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ የክትትልና የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል፡፡ የጎንደር ከተማ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ወርቁ በበኩላቸው በከተማው ቱሪስቶችንና እንግዶችን የሚያዝናኑ 10  የባህል ምሽት ቤቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። "በአንዳንድ ምሽት ቤቶች የሚስተዋለውን የስነ-ምግባር ችግር ለመቅረፍ መምሪያው ህጉን ተከትሎ እርምጃ በመውሰድ ለማስተካከል ጥረት ያደርጋል" ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል በዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ህጋዊ የንግድና የሙያ ፈቃድ የተሰጣቸው ከ300 በላይ የባህል ምሽት ቤቶች እንደሚገኙ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም