አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዛል

170

ኢዜአ፤ ታህሳስ 21/2012 አዲስ የተሻሻለው የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዛል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ዛሬ ውይይት አድርገዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ እንዳሉት የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ አጠቃላይ የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽእኖ በጥንቃቄ በማጤን የተዘጋጀ ነው።

 

ኢትዮጵያ እያደረገች ባለው የምጣኔ ሃብት ሽግግር ውስጥ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም በተዘጋጀው ኤክሳይስ ረቂቅ አዋጅ ትራክተርን ጨምሮ የግብርና መሳሪያዎች ሙሉ ለሙሉ ከቀረጥ ነጻ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዚህም ለዘመናት በባህላዊ መንገድ እየተካሄደ ያለውን የኢትዮጵያን ግብርና በማዘመን ምርታመነትን ለመጨመር አዋጁ ስራ ላይ ሲውል እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።

የገቢዎች ሚኒስትር አዳነች አበቤ በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ ስራ ላይ ሲውል የገቢ አሰባሰብ አስተዳደርን በማሻሻል ያግዛል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ አዋጁ እኩል ተጠቃሚነትን በማምጣት በኩልም እገዛ ያደርጋል።

ኢትዮጵያ ከኤክሳይዝ ታክስ እያገኘች ያለው ገቢ አንድ በመቶ እንደማይሞላ በማንሳት ይህም ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነጻጻር ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ማሻሻያ ሳይደረግበት የቆየው አዋጅ መሻሻሉ በምጣኔ ሃብትና ማህበራዊ የህብረተሰብን ተጠቃሚነት ለማምጣት ያግዛል ብለዋል።

የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በማስፈን ዝቅተኛ የማህበረሰብ ክፍልን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

አዋጁ ጸድቆ ተግባራዊ ሲደረግም ለስነ ጥበብ እድገት ሲባል የቴሌቪዥንና ቪዲዮ ካሜራዎች ላይ ተጥሎ የነበረው 40 በመቶ ኤክሳትይዝ ታክስ ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉንም ገልጸዋል።

አዋጁ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራ ሲሆን በቀጣይ ከተለያዩ የህብረተሰብና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ይደረጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም