በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ህፃናትን ችግር ለመፍታት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

1493

ታህሳስ 21 / 2012 በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ህፃናትን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ።
የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር  በደቡብ ክልል ከዞን ሴክተር መስሪያ ቤቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ዛሬ በሀዋሳ ምክክር አካሂዷል ፡፡

የሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ በምክክር መድረኩ እንደገለጹት በሀገር ደረጃ በርካታ ህፃናት በተለያዩ ምክንያቶች አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ።

“በተለይ ኑሯቸውን በከተሞች ጎዳናዎች ላይ ያደረጉት ህፃናት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት ካለመቻላቸውም በላይ ከአካልና አእምሯቸው ጋር የማይመጣጠን ከባድ ሕይወት ለመምራት ይገደዳሉ” ብለዋል።

ህፃናቱ በዕድሜና ፆታቸው ምክንያት በሚፈጸምባቸው ጥቃትና መገለል ለአካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳቶች እንደሚዳረጉ ተናግረዋል ።

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት በሚገጥማቸው ውስብስብ ችግሮች ምክንያት ለአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነትና ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተጋላጭ ይሆናሉ።

ችግሩ ማህበራዊ ቀውስን ከማባባስ ባለፈ በሀገር ገፅታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተለ ነው።

ህፃናቱ ያሉባቸውን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ህብረተሰቡም በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠቁመዋል፡፡

ማህበራዊና ባህላዊ አደረጃጀቶችን እንዲሁም የልማት ቡድኖችና ባለሀብቶችን በማስተባበር ህፃናቱ ድጋፍ እንዲገኙ ማድረግ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የላቀ ሚና እንዳለው አመላክተዋል።

ሚኒስቴሩ በህፃናት መብትና ደህነንነት ላይ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የደቡብ ክልል ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ባትሪያ ቦሮዳ በበኩላቸው በክልሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህፃናት ለጎዳና ህይወት፣ ለህገ-ወጥ ዝውውርና ጉልበት ብዝበዛ እንደሚጋለጡ ተናግረዋል ፡፡

በተለይ ወላይታና ሲዳማ ዞኖች ላይ ችግር በስፋት እንደሚስተዋል ጠቅሰዋል።

ቢሮው ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናትን ከጎዳና የማንሳትና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማቀላቀል ሥራ እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

“ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ባለመቻሉ አሁንም ህፃናት ተመልሰው ወደ ጎዳና ህይወት ይቀላቀላሉ”ብለዋል።

ህፃናቱ በኑሮ ችግር፣ አቻ ግፊትና ህገ-ወጥ ደላሎች በመታለል ከአካባቢያቸው ርቀው ለመሄድ እንደሚገደዱ አመልክተዋል።

ችግሩን ከመነሻው ለማስቆም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር ጥናት ማካሄዱን ተጠቁመዋል።

በጥናቱ መሰረት ህፃናቱ ወደ ቤተሰቦቻቸው ከተቀላቀሉ በኋላ ተመልሰው የሚፈልሱበትን ሁኔታ ለማስቀረት የቤተሰቦቻቸውን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከእድሮችና ባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ህፃናት እገዛ እንዲገኙ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል ፡፡

በምክክር መድረኩ የፌዴራል፣ የክልል እና ዞኖች ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተሳትፈዋል ፡፡