በሰው ሕይወት መጥፋትና በአካል ጉዳት ጥፋተኛ የሆኑ ሁለት የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በ24 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጡ

81
ኢዜአ ታሀሳስ 21 /2012 በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ሁከትና አመጽ በመቀስቀስ ለሁለት ተማሪዎች ሕይወት መጥፋትና በአንድ ተማሪ ላይ ለደረሰ ከባድ የአካል ጉዳት ጥፋተኛ የተባሉ ሁለት ተማሪዎች እያንዳንዳቸው በ24 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት አስታወቀ ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው በዩኒቨርሲቲው የ1ኛ ዓመት ተማሪ በሆኑት አማኑኤል ማሞ አብዲሳ እና ፈይሳ ፍቃዱ ዋቅጋሪ ላይ ነው። ተማሪዎቹ የተፈረደባቸው ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሁለት ተማሪዎችን ደብድበው መግደላቸው በመረጋገጡ መሆኑን መሀል ዳኛው ተናግረዋል። መሀል ዳኛው አቶ ግርማ ደቻሳ ለኢዜአ እንዳሉት ተማሪዎቹ ሰኔ 24 ቀን 2ዐ11ዓ.ም ከምሽቱ 4፡ዐዐ ሰዓት ላይ በፍቼ ከተማ በሚገው ጀኔራል ታደሰ ብሩ ካምፓስ በተማሪዎች መካከል ሁከትና አመፅ ቀስቅሰዋል። በእዚህም ለሁለት ተማሪዎች ሕይወት መጥፋትና ለአንድ ተማሪ ከባድ የአካል ጉዳት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ጉዳትና ውድመት እንዲደርስ ማድረጋቸው በአቃቤ ህግ ማስረጃ ተረጋግጧል። ግለሰቦቹ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ለህገወጥ ድርጊት በሚያነሳሳ ቅስቀሳ ምክንያት በተፈጠረ ሁከት ሁለት ሟቾችን በአሰቃቂ ሁኔታ በድንጋይና በብረት ደብድበው ሕይወታቸው እንዲጠፋ ምክንያት መሆናቸውና ድርጊቱን መፈፀማቸው በአቃቤ ህግ ማስረጃ ቀርቦባቸው በቂ የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን እንደወሰነባቸው ዳኛው አቶ ግር ተናግረዋል። ተከሳሾቹ ጥፋተኛ የተባሉበት የህግ አንቀፅ ከ5 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ፤ ጉዳዩ ከባድ ከሆነ ደግሞ በሞት ፍርድ እንደሚያስቀጣ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አመልክቷል። ሁለቱ ተከሳሾች ከዚህ በፊት የቅጣት ሪከርድ የሌላቸውና ያለፈ ሕይወታቸው መልካም እንደነበር ዳኛው ጠቁመው፣ ድርጊቱን በወጣትነት ስሜትና በአፍራሽ ተልኮ ተነሳስተው የፈጸሙት መሆኑን አስታውቋል። የዞኑ ፖሊስ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንስፔክተር ተስፋዬ ወርቁ በበኩላቸው እንዳሉት በሁከቱ  ምክንያት በወቅቱ በዩኒቨርሲቲው አንዳንድ የመኝታ ክፍሎች መስኮትና የበር መስታወቶች ላይ የመሰባበር አደጋ ደርሷል። በተማሪዎቹ የተፈፀመው የወንጀል ድርጊት እጅግ አሳዛኝ መሆኑን የገለጹት የህግ ባለሙያ አቶ ማሞ በላቸው በበኩላቸው መንግስት በህገ ወጦች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ እንዲጠናከር ጠይቀዋል። የተሰጠው ፍትህም የሚያስተምር መሆኑን ነው የገለጹት። በተለያየ ጊዜና ቦታ በአንዳንድ ተማሪዎች ላይ የሚከሰተው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ችግር ወላጆችን ስጋት ውስጥ የከተተ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ጠጂቱ አዱኛ የተባሉ የፍቼ ከተማ ነዋሪ ደግሞ "ህዝቡ ከተማሪዎች የሚጠብቀው ኃላፊነት የተሞላበት ተግባር ነው" ብለዋል። ተመሳሳይ ድርጊት ዳግም እንዳይፈፀም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ ወላጆችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተማሪዎችን መምከርና ማነፅ እንዳለባቸው አመልክተዋል። የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ  እሸቱ ያደታ በበኩላቸው የትኛውም ወንጀል ሲፈፀም ህብረተሰቡ ወንጀለኞችን ለህግ አሳልፎ በመስጠትና እውነትን በመመስከር የህግ የበላይነት እንዲሰፍን የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ። በሁለቱ ተማሪዎች ላይ የተወሰነው የቅጣት ውሳኔ ወንጀል ፈፃሚ አካላት በቡድንም ሆነ በተናጠል የሚፈፅሙት ድርጊት ከቅጣትና እስራት እንደማያድን አውቀው ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስተማሪ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ የወንጀል ድርጊት ተከሰው የቀረቡ ሌሎች ስድስት ተማሪዎች ከጥርጣሬ ውጪ በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ  ምንም መከላከያ ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም