ታዳጊ ህጻናትና ወጣቶችን ከአደንዛዥ ዕጽ ሱስ ለመታደግ የመዝናኛ ቦታዎችና ቤተ መጻሐፍት ሊበራከቱ ይገባል ተባለ

169
ኢዜአ ታህሳስ 18/2012.. ታዳጊ ህጻናትና ወጣቶች የአልኮል መጠጥን ጨምሮ የአደንዛዥ እጽ ተጠቃሚ አንዳይሆኑ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው ቤተ መጸሐፍት እና የመዝናኛ ስፈራዎች ሊበራከቱ ይገባል ሲሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ። የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎች በመገናኛ ብዙሃን እንዳይተላለፉ መደረጉ መልካም ጅማሮ መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል። በአንዳንድ ጥናቶች መሰረት በኢትዮጵያ በተለይም በከተሞች አካባቢ ወጣቶች የአልኮል መጠጥን ጨምሮ በአደንዛዥ እፅ ሱሰኝነት በመጋለጥ ላይ ናቸው። ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉትም በርካታ ታዳጊ ህፃናትና ወጣቶች በአደንዛዥ እፅና በሌሎች መጤ ልማዶች በስፋት እየተጠመዱ መምታቸውን መታዘባቸውን ይናገራሉ። ወጣቶቹን ከአደንዛዥ እፅ ተጋላጭነት በመከላከልና ቀጣይ ህይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ  ቤተሰብና  ማህበረሰብ ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት የመዝናኛ ቦታ እና ቤተ መጻፍት መስፋፋት አለባቸው ሲሉም ያክላሉ። ታደጊ ህጻናትና ወጣቶች እድገታቸው  ከሱስ የጸዳ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ ማህበረሰባዊ ተቋማትና መሰባሰቢያ ማእከላት ውስን መሆናቸውንም ጠቅሰው ይህንን ለመለወጥ የሚደረገው ጥረት በሚገባው መጠን መስፋት እንዳለበት ያሳስባሉ። ወጣቶች  በሱስ ምክንያት የሚደርስባቸውን  ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥም  የወላጅ፣ የማህበረሰብና  የባለድርሻ አካላት ጠንካራ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ። ባለሃብቶችና አቅም ያላቸው የትምህርት ተቋማት ወጣቶችን  ከመጤ ልማዶችና አደንዛዥ እጽ ሱሰኝነት ለመታደግ ምቹ ሁኔታዎችን  በመፍጠር  የበኩላቸው  እንዲወጡም  አሰተያያት ሰጪዎቹ  ጠይቀዋል። በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ  የተለያዩ ማስታወቂያዎች ትውልድን ለመጥፎ ነገር የሚያነሳሱና አስፈላጊ ወደ አልሆነ መንገድ የሚመሩ በመሆናቸው ጥንቃቄ ያስፈልጋልም ብለዋል። የመጠጥ ማስታወቂያዎች በመገናኛ ብዙሃን አንዳይተላለፉ መደረጉ መልካም ጅማሮ በመሆኑ ተግባሩ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚመለከተው አካል ቁጥጥሩን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም