በደቡብ ክልል የትራኮማና የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ እንክብልና ክትባት በዘመቻ ተሰጠ

72
ኢዜአ ታህሳስ 18/2012 በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ቡርጂና አማሮ ልዩ ወረዳዎች የትራኮማና የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ እንክብልና ክትባት በዘመቻ ተሰጠ። በጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መስፍን ዱቤ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የትራኮማ በሽታን ለመከላከል ከታህሳስ 6/2012ዓ.ም ጀምሮ ለስምንት ቀናት የመድኃኒት እደላ በዘመቻ ተካሄዷል። የመድኃኒት እደላውን ያከናወኑት ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ  ከተባለ ድርጅት ጋር  በመተባበር ነው። ህብረተሰቡ የግልና የአካባቢ ንጽህናን በመጠበቅ በሽታውን ለመከላከል እንዲቻል እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የጌዴኦ ቡርጂና አማሮ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ውብሸት መኩሪያ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በዞኑና በልዩ ወረዳዎቹ የዓይን ህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል። "ዝክሮ ማክስ " የተሰኘው የትራኮማ በሽታ መከላከያ እንክብል በጌዴኦ ዞን ስምንት ወረዳዎች እንዲሁም  በአማሮና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች መሰጠቱን ጠቁመዋል። በዘመቻውም በዞኑና በልዩ ወረዳዎቹ የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን 300ሺህ  በላይ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ የእናቶችና ህጻናት ስርዓተ ምግብ አስተባባሪ አቶ ማርቆስ ደያሶ እንደገለጹት 14 ዓመት ለሞላቸው 19 ሺህ ልጃገረዶች የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ተሰጥቷል። ክትባቱ በዞኑ በሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ቤት ለቤት በመዘዋወር እንደተሰጠ አመክተዋል። በሁለት ዙር የሚሰጠው ይህ የመከላከያ ክትባት ቀሪው  ከስድስት ወራት በኋላ እንደሚፈጸም  ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም