ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የምጣኔ ኃብትና የልማት ትብብር ግንኙነት በመጪው አዲስ ዓመትም አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለፀች

94
ኢዜአ ታህሳስ  17/2012 የቻይና መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የጀመረውን የምጣኔ ኃብትና የልማት ትብብር ግንኙነትን በመጪው የግሪጎርያን አዲስ ዓመትም የበለጠ በማስፋት አጠናክሮእንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር አስታወቁ።

የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ የቻይና-አፍሪካ ቀርከሃ ልማት ማእከል ለመክፈት የአዋጭነት ጥናት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን የሁለቱን አገሮች ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደሩ በመግለጫቸው በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለው የልማት ትብብርና የምጣኔ ኃብት ግንኙነት አሁንም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መሆኑን ገልፀዋል።

እየተጠናቀቀ ባለው የግሪጎርያውያኑ 2019 በኢትዮጵያ በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተመዘገቡት የቻይና ኩባንያዎች 147 መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም በ2019 ውስጥ ወደኢትዮጵያ ከገባው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ውስጥ 60 በመቶውን እንደሚይዝ አምባሳደር ታን ጂያን አመልክተዋል።

ይህ አፈፃፀም መዋእለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ በማፍሰስ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩት ቻይናዊያን ቁጥር በየዓመቱ ከ12 በመቶ በላይ እድገት እያሳየ መምጣቱን የሚጠቁም ነው ብለዋል።

ጨርቃጨርቅ፣ የመድሃኒት ፋብሪካዎች፣ የህንጻ ግንባታ ቁሳቁሶች፣ ብረታብረትና ሴራሚክስ የቻይና ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ከተሰማሩባቸው ዘርፎች መካከል ይገኙበታል።

የቻይና መንግስት የኢትዮጵያን አጠቃላይ የልማት ዘርፍ ለማገዝ ከሚያደርጋቸው የተለያዩ ጥረቶች መካከል የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ዋነኛ በር የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ፕሮጀክት ወደሥራ ገብቶ በአገሪቱ የምጣኔ ኃብት መስተጋብር ላይ ዓይነተኛ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

''የምድር ባቡሩ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት በአገሪቱ ከሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርቶች የውጭ ገበያን እያሳደገው መጥቷል፤ አሁን ባለው መረጃ መሰረትም በዚህ የምጣኔ ኃብት መንቀሳቀሻ ኮሪደር በኩል የሚካሄደው ዓመታዊው የወጪ ንግድ መጠን 110 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል'' ብለዋል።

ይኸው የእድገት መጠን በየዓመቱ በ35 በመቶ እያደገ መሆኑን በመጠቆም።

''የተለያዩ የቻይና ኩባንያዎች በሶማሌ ክልል እየተካሄደ ባለው የነዳጅ ፕሮጀክት ልማት ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት አምባሳደር ታን ጂያንግ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ መንደር ለመገንባት በተጀመረው ፕሮጀክት ላይም ተሳታፊ ናቸው'' ብለዋል።

የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ የቻይና-አፍሪካ ቀርከሃ ልማት ማእከል ለመክፈት ጥናት የአዋጭነት ጥናት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑም አምባሳደሩ ይፋ አድርገዋል።

አምባሳደሩ በዚሁ መግለጫቸው እንዳሉት፤ በመጪው አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ የቻይና-አፍሪካ ቀርከሃ ልማት ማእከል ለመገንባት የሚያስችል የአዋጭነት ጥናት ይካሄዳል።

ግንባታንና መገልገያ ቁሳቁስን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎት የሚውለው ቀርከሃ በተለይ በኢትዮጵያ በከፍተኛ መጠን ሊመረት የሚችልና አገሪቱም በዘርፉ ከአፍሪካ ትልቅ ኃብት ያላት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቀርከሃ ምርትን በማሳደግ ለውጭ ገበያ ጭምር ማቅረብ ከተቻለ ዘርፉ የኢትዮጵያን ምጣኔ ኃብት ለማሳደግ ያግዛልም ብለዋል።

የኢትዮጵያን የግብርና ልማት በማዘመን የአገሪቱን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ይቻል ዘንድ ቻይና እየሰጠች ያለውን የቴክኒክና ሌሎች ድጋፎችም አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉም አምባሳደሩ አስታውቀዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ ዋነኛ ምግብ የሆነውን ጤፍ ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰጠ ያለውን የቴክኖሎጂ ድጋፍ ለአብነት ጠቅሰዋል።

ለአፍሪካ አገሮች ግልጋሎት የሚሰጥ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማእከል በአዲስ አበባ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልፀዋል።

በአጠቃላይ የቻይና መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ጠንካራና ሰፊ የምጣኔ ኃብትና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ይሰራል ሲሉ ነው አምባሳደሩ የገለፁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም