የህብረተሰቡ አብሮ የመኖርና የአንድነት እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንሰራለን ... የምስራቅ ሐረርጌ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ

162

ኢዜአ፤ ታህሳስ 17/2012 የህብረተሰቡን አብሮ የመኖርና የአንድነት እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስታወቀ።

ሰሞኑን በሞጣ ከተማ አስተዳደር በእምነት ተቋማት ላይ የሰረሰውን ጥቃት ጉባዔው አውግዟል።

ትናንት በሐረር ከተማ የዞኑ የሰላምና ደህንነት አስተዳደር ጽህፈት ቤት የጉባዔው አባላት ባካሄዱት ውይይት ማጠቃለያ ባለ 8 ነጥብ የአቋም  መግለጫ አውጥተዋል።

በአቋም መግለጫው የህብረተሰቡን አብሮ የመኖርና የአንድነት እሴት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በህብረተሰቡ መካከል የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመቻቻልና የመረዳዳት ባህል እንዲጎለብት በየእምነት ተቋማቱ የማስተማር ስራን እንደሚያጎለብቱም ገልጸዋል።

በምስራቅ ጎጃም ሞጣ ከተማ  በእምነት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጥቃት የማናቸውንም እምነት የማይወክል መሆኑንና ተግባሩንም በጽኑ እንደሚቃወሙት ተናግረዋል።

በእምነት ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እና ድርጊቶቹ ሲፈጸሙ በቸልታ የሚመለከቱ አመራሮችና የህግ አካላት እንዲጠየቁ  በመግለጫው ጠቅሰዋል።

አንድ አንድ ሐላፊነት የጎደላቸው አካላት በሚዲያና በሌሎች መንገዶች ከሚያሰራጩት ጠብ ጫሪ ተግባራት እንዲቆጠቡና ጉዳት የደረሰባቸው የእምነት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም መንግስት አስፈላጊው ድጋፍ እንዲያደርግ በመግለጫቸው ጠይቀዋል።

የጉባዔው ሰብሳቢ ሼህ ዛሂር አብዱልከሪም ″በቤተ እምነቶቹ ላይ የደረሰው ጉዳት እጅግ የሚያሳዝንና ተግባሩ በሁሉም ዘንድ የሚወገዝ ነው″ ብለዋል፡፡

የእምነት ተቋማትን በማቃጠልና ሀብረተሰቡን በማጋጨት ስልጣን መያዝ መሞከር ለማንም የማይጠቅም በመሆኑ በዚህ ተግባር የተሰማሩ አካላት ከተግባራቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

''መንግስትም ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን ለህግ ማቅረብና የፍርድ ውጤቱን በይፋ መግለጽ ይገባዋል'' ብለዋል።

''በቤተ እምነት ላይ ሚደርሰው ጥቃት  የሀይማኖት አባቶችን ያሳዘነና በየትኛውም የእምነት ተከታይ የሚወገዝ ተግባር ነው'' ያሉት ደግሞ የጉባዔው ፀሐፊ ፓስተር አንዱአለም ሞላ ናቸው፡፡

በቤተ እምነቱ ላይ በተከሰተው ውድመት እጅግ ማዘናቸውንም ገልጸዋል።

መንግስትም ጥፋተኞቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እንዲያቀርባቸውና  ለቤተ እምነት ጥበቃ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም