በአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት ሊያቃልል የሚያስችል የጉዞ እቅድ መተግበሪያ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

3866

ኢዜአ፤ ታህሳስ 17/2012 በአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት መረጃን ለመስጠት የሚያስችል የጉዞ እቅድ መተግበሪያ ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ‘ወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት’ ከተባለ ተቋም ጋር በመተባበር የትራንስፖርት አገልግሎቱን በማዘመን መረጃን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የጉዞ እቅድ መተግበሪያ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የትራንስፖርት ዘርፍን በማሻሻል ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

አዲስ አበባ የዲፕሎማትና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ ከህዝቡ ብዛት ጋር የሚመጣጠን የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ዘርፉን ማዘመን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

”በተለይም ተጠቃሚዎች ወደሚፈልጉት ስፍራ ለመድረስ አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል መረጃ ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል።

በመሆኑም ከወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን የተዘጋጀው መተግበሪያ የማህበረሰቡን የትራንስፖርት አማራጭ ለማሳደግ የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል።

የኢንስቲትዩቱ ጂአይኤስ ኢንተርን ባለሙያ አቶ ረብራ ሂርጳ በበኩላቸው መተግበሪያው የትራንስፖርት ተጠቃሚ ማህበረሰቡ ቀልጣፋና አማራጭ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል የመረጃ ቋት መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይም በአዲስ አበባ  እንደ ሸገር፣ አንበሳ አውቶቡስና መካከለኛ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለደንበኞች መረጃ በመስጠት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል በስማርት ስልክ የሚተገበር እንደሆነ ጠቁመዋል።