አማራና ትግራይ በፍቅርና በአንድነት የኖሩ፤ ወደፊትም የሚኖሩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው-የአገር ሽማግሌዎች

192
ኢዜአ ታህሳስ 16/2012 አማራና ትግራይ ጦር የሚማዘዙ ሳይሆኑ በፍቅርና በአንድነት የኖሩ፤ ወደፊትም የሚኖሩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ሲሉ የሁለቱ ክልል ተወካይ የአገር ሽማግሌዎች ተናገሩ። 'ፍትህ ለሁሉም' ከኢትዮጵያ የአገር ሽማገሌዎች መማክርት ጋር በመተባበር በሁለቱ ክልሎች ሰላም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ዛሬ አካሂዷል። የምክክር መድረኩ ማምሻውን ሲጠቃለል የአገር ሽማገሌዎች መግለጫ ሰጥተዋል። ዛሬ በተደረገው የውይይት መድረክ ሽማግሌዎቹ በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ስለችግሩ መንስኤና የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ የመከሩ ሲሆን በማጠቃለያውም በሁለቱም ህዝብ መካከል ቅራኔ እንደሌለ ተመልክቷል። ይልቁንስ የፖለቲካ ልሂቃን፣ አንቂዎችና መገናኛ ብዙሃን ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት መሆናቸውን የማንነት ጥያቄዎችና ዩኒቨርሲቲዎችም ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆናቸው ተጠቅሷል። በምክረ ሃሳብ ደረጃም የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ወደክልሎች በማምራት የመንግስት ሃላፊዎችን እንዲያነጋግሩ፣ የፖለቲካ ልዕሂቃንን እንዲመክሩ፣ የማንነት ጉዳዮች ለህግና ታሪክ ሰዎች በመተው ወጣቶችና የድንበር አካባቢ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የህዝብ ለህዝብ መድረክ ማዘጋጀት የሚል ሃሳብ ቀርቧል። ከሁለቱም ክልሎች የተወከሉ የአገር ሽማግሌዎችም የመግለጫው መልክት ያስተላለፉ ሲሆን በመልክታቸው የሁለቱ ክልል ህዝብ ለሺ ዘመናት በመከራም ሆነ በተድላ ጊዜያት በቤተሰባዊ አብሮነት ታሪክ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። ወደፊትም ከሁለቱም ወገን ህዝብ አንዱ በሌላው ላይ ጦር የሚማዘዝ ሳይሆን በሰላም የሚኖር ህዝብ እንደሆነ አረጋግጠዋል። ከአማራ አገር ሽማገሌዎች ተወካይ አቶ ባዬ በዛብህ እንዳሉት የአማራና የትግራይ ህዝብ በአገር ግንባታ፣ በኢትዮጵያ ዳር ድንበር ጥበቃ፣ በአርበኝነቱም በአብሮነት የሞተ አንድ ህዝብ መሆኑን ገልጸዋል። መሰረት በሌለው ጊዜ ወለድ ችግር ቅራኔ ውስጥ እንደማይገባ ገልጸው፣ ችግሩን ለመፍታትም እንደሚሰራ ተናግረዋል። የትግራይ አገር ሽማግሌዎች ማኅበር ሰብሳቢ መልዓከ ጸሃይ ተሻለ ገብረስላሴ በበኩላቸው ትግራይና አማራ በየትኛውም ዘመን አንዱ በአንዱ ላይ ተነስቶ የማያቅ ፣ ለሺህ ዓመታት በአብሮነት የዘላቀ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ብለዋል። ወደፊትም ፖለቲከኞች እንደሚነዙት ሳይሆን በቤተሰባዊነት አብሮነት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም