ዳሽን ባንክ የማህበራዊ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት መርሃ-ግብር ይፋ አደረገ

84

ኢዜአ ታህሳስ  16 /2012 ዳሽን ባንክ ሁሉንም የአገሪቱን ዜጎች የሚያሳትፍ ግዙፍ የማህበራዊ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት መርሃ-ግብር ዛሬ ይፋ አድርጓል።

"የኢትዮጵያ ታለንት ፓዎር ሲሪየስ " በሚል ስያሜ የተቀረፀው ፕሮጀክቱ ሥራ ፈጠራን በማበረታታት  ክህሎት ላላቸው ዜጎች የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

የሥራ ፈጠራ ስልጠና፣ የጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አቅም ግንባታ፣ የከፍተኛ ትምህርት የፋይናንስ ድጋፍ መርሃ-ግብር፣ የፋይናንስ ተደራሽነት መርሃ-ግብር፣ የቢዝነስ ክለብ ምስረታ፣ የገበያ ትስስርና የእሴት ሰንሰለት የፋይናንስ ድጋፍ የፕሮጀክቱ ዓላማዎች ናቸው።

በተለይም የሥራ አጥነትን በመቀነስ ድህነትን ለማስወገድ ለሚደረገዉ አገራዊ እንቅሰቃሴ ፕሮጀክቱ  ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

በፕሮጀክቱ መሠረት በዚህ ዓመት በተመረጡ ስድስት ከተሞች የሚገኙ ዜጎች ተመልምለው የሥራ ፈጠራ ክህሎትና የአቅም ግንባታ ሥልጠና ይሰጣቸዋል።

ሥልጠናዉን የሚወስዱ ዜጎችም በአማካሪ ድርጅት እየታገዙ የቢዝነስ ክለብ እንዲያቋቁሙና ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ድጋፍም ከባንኩ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ተገልጿል።

በተጨማሪም ባንኩ የሚያከናውናቸው ተግባራት መንግስት ከቀየሰው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ትግበራ አንጻር ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ተገልጿል።

በሌላ በኩል ባንኩ በቴሌቪዥን ስርጭት በየሳምንቱ የሚተላለፍ በሥራ ፈጠራና ቢዝነስ ክህሎት ዙሪያ የሚያጠነጥን ሳምንታዊ ፕሮግራም ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑንም አስታውቋል።

የውድድሩ አሸናፊዎችም የማበረታቻ ሽልማት የሚበረከትላቸው ሲሆን፤ ከተወዳዳሪዎቹ መካከል አሸናፊ ሀሳብ ያቀረቡ ሥራ ፈጣሪዎች ደግሞ ወደፊት ለመጀመር ለሚያስቡት የንግድ ሥራ የፋይናንስ ድጋፍ በባንኩ ይደረግላቸዋል ተብሏል።

ዳሸን ባንክ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ በማስተዋወቅ ረገድ ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ይነገርለታል።

በአገሪቱም የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ካርድን ጨምሮ በርካታ ዘመናዊ የባንክ አሠራሮችን አስቀድሞ ይፋ ያደረገው መሆኑም ተጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም