በትግራይና አማራ ክልል ፖለቲከኞች መካከል የተፈጠሩ ጊዜያዊ አለመግባባቶች ከወዲሁ ሊፈቱ ይገባል - የሰላም ሚኒስቴር

82

ኢዜአ ታህሳስ 16 ቀን 2012 "በትግራይና አማራ ክልል አንዳንድ ፖለቲከኞች መካከል የተፈጠሩ ጊዚያዊ አለመግባባቶችን ተነጋግረን ልንፈታ ይገባል" ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን አሳሰቡ።

"የውስጥ ችግራችንን ተነጋግረን ሳንፈታ ቀርተን ሀገር አደጋ ላይ ከወደቀች የታሪክ ተወቃሽ እምንሆነው እኛው ነው" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

የሁለቱን ክልሎች የሃገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች የተሳተፉበትና  በግጭት አወጋገድና ሰላም ግንባታ ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር በሁለቱ ክልሎች የፖለቲካ ሰዎች መካከል የተፈጠረውን ጊዜያዊ አለመግባባት ለመፍታት የአገር ሽማግሌዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተጀመረው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ መቀጠል የሚችለው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ በመነጋገር መፍታት ሲቻል ነው ብለዋል።

ለዚህም የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና መላው ህዝብ በትጋት መስራት ይጠበቅበታል  ሲሉም አሳስበዋል።

አክለውም "ይህ ሳይሆን ቀርቶ አገር አደጋ ላይ ከወደቀች ዛሬ ላይ ለሚፈጠረው ማንኛውም መጥፎ አሻራ የታሪክ ተወቃሽ እንሆናለን" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

አለመግባባቱ የተፈጠረው በሰፊው የክልሎቹ ህዝቦች አለመሆኑን የአገር ሽማግሌዎቹ በበኩላቸው ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህ አለመግባባት ይፈታ ዘንድ የበኩላቸውን ሚና ለመጫወት የአገር ሽማግሌዎቹ ቃል ገብተዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ ህዝብ በአብሮነትና በአንድነት የሰራቸውን መልካም ታሪኮች ለትውልድ በማሸጋገር፤ ከልዩነቱ በላይ ስለ አንድነቱ እንዲማር ለማድረግ እንደሚሰሩ ነው የአገር ሽማግሌዎቹ የገለፁት። አገሪቱ ወዳልተገባ አቅጣጫ እንድትሄድ መፍቀድ የለብንም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም