የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ ማለዳ ላይ አዲስ አበባ ገብተዋል

60

ኢዜአ ታህሳስ 15 / 2012 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኤርትራውን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ጉዳይ ላይ መክረዋል።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ ማለዳ ነው አዲስ አበባ የገቡት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀውን የሻከረ ግንኙነታቸውን መቅረፋቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም ወደ አሥመራ ተጉዘው  በሁለቱ አገሮች መካከል ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት የሚያሻሽሉ ስምምነቶችን መፈራረማቸው ይታወሳል።

በወቅቱ ኤርትራውያን በነቂስ ወጥተው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ከጥቂት ቀናት በኋላም የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው መክረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወንድማማች የሆኑትን የኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝቦች በማገናኘትና አገራቱ አቋርጠውት የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማስጀመር ረገድ ላደረጉት ጥረት የ2019  የሰላም ኖቤል ሎሬትነትን አግኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ሽልማቱን ሰላም ወዳዱን የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝብን ወክለው እንደሚቀበሉት ገልጸው፤ በተለይ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሁለቱ አገሮች ሰላማዊ ግንኙነት ላበረከቱት አስተዋዕኦ ምስጋና ማቅረባቸው ይታወሳል።

በተጨማሪ በሁለቱ አገሮች የእርስ በርስ ጦርነት ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ህይወት መቅጠፉን፣ በሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለአካል ጉዳት መዳረጉን  በንግግራቸው አስታውሰዋል።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማት ሽልማቱን አስመልክተው በሰሩት ዘገባ ሽልማቱ ለረዥም ዓመታት በግጭት ቀጠና ውስጥ ሲታመስ የቆየው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ወደ ሰላም ለመመለሱ ትልቅ ማሳያ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም