ለብልጽግና ፓርቲ ህጋዊ ዕውቅና ተሰጠ

63
ኢዜአ ታህሳስ  15 /2012 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለውህዱ ብልጽግና ፓርቲ ህጋዊ ዕውቅና መስጠቱን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእውቅና ጥያቄና የፓርቲ መለያ ሰንደቅ አላማ የማጽደቅ ጥያቄ ያቀረቡ ፓርቲዎችን ጉዳይ አይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል። የኢህአዴግ አባል የነበሩ ሶስት ፓርቲዎች እና ሌሎች አምስት ፓርቲዎች በጋራ ራሳቸውን በማክሰም ውህድ ብልጽግና ፓርቲን መመስረታቸውን በማሳወቅ የእውቅና ምስክር ወረቀት እንዲሰጣቸው ለቦርዱ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል። ቦርዱ የእውቅና ጥያቄ ከቀረበለት በኋላ በተጨማሪ ማሟላት ያለባቸውን ሰነዶች እንዲያሟሉ በታህሳስ 01 ቀን 2012 ዓ.ም ጥያቄ አቅርቧል። በቀረበው ጥያቄ መሰረት ታህሳስ 06 ቀን 2012 ዓ.ም ምላሾችና ማብራሪያዎች ተሟልተው መቅረባቸውን በማረጋገጡ ብልጽግና ፓርቲን ውህድ ፓርቲ ሆኖ ስለመመስረቱ ህጋዊ የምስክር ወረቀት እንዲሰጥ ዛሬ ወስኗል። ቦርዱ የፓርቲውን ጥያቄ በፓለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ አዋጅ 1162/2011 መሰረት መርምሮ ውሳኔ መስጠቱንም ነው የገለጸው። ብልጽግና ፓርቲ፤ በቅርቡ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ( ኦዴፓ)፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን)የሃረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ)፣ አማራ ዴሞክራያዊ ፓርቲ ( አዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ)፣ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ)፣ የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ፓርቲ (ጋህአዴን)የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ( ቤጉህዴፓ) በውህደት የመሰረቱት ነው። ውህዱ ፓርቲ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 92/2 መሰረት በተመዘገበ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ውህደቱ ያስገኘውን ሃብትና ንብረት እና እዳ የሚያሳይ የሂሳብ ሪፓርት ለቦርዱ እንዲያቀርብ በውሳኔው ውስጥ መካተቱን የቦርዱ የኮሚኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ ለኢዜአ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም