በአማራ ክልል የቱሪስቶችን መዋከብ ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ ነው

86
ኢዜአ ታህሳስ 15 / 2012 በአማራ ክልል በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች የሚስተዋለውን የጎብኝዎች መዋከብ ለማስቀረት ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ። በቱሪዝም ዘርፉ የሚስተዋለውን ህገ ወጥነት ስርዓት ለማስያዝ በሚቻልበት ሁኔታ የምክክር መድረክ በባህርዳር ከተማ ተካሂዷል። የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ በመድረኩ እንዳሉት ክልሉ ብዛት ያለው ሰው ሰራሽ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የመስህብ ሃብቶችን አካቶ የያዘ ነው። የቱሪዝም ሃብቱን በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ  በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ሃብት ለማሳደግ በተከናወነው ስራ  የቱሪስት ፍሰቱ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። ሆኖም  በባለድርሻ አካላት የቅንጅት መጓደል ክልሉ ባለው የቱሪዝም ሃብት ልክ ተጠቃሚ እየሆነ አይደለም። በተለይም በመዳረሻ ስፍራዎች እየተስተዋለ ያለው የቱሪስቶች ወከባና አግባብ ያልሆነ የክፍያ ጥያቄ ዘርፉን እየጎዳው መሆኑን አመልክተዋል። በዘርፉ ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሆኑ አስጎብኝ ማህበራት፣ ባለሆቴሎችና ሌሎች አካላትን በማስተባበር ሰላምና የተረጋጋ የቱሪስት ፍሰት እንዲኖር ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም መጪው የገናና በቅርቡ በዩኒስኮ እንደሚዘገብ የተወሰነው  የጥምቀት በዓል ለመታደም ከተለያዩ  ሃገራት ጎብኚዎች ወደ ክልሉ ስለሚመጡ ሁሉም የቱሪዝም አምባሳደር ሆኖ ሊሰራ እንደሚገባ ዶክተር ሙሉቀን አሳስበዋል። የቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አዳም በመድረኩ ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳለመለከቱት በሃገሪቱ ካሉት የቱሪዝም ሃብቶች 40 መቶ በአማራ ክልል ይገኛሉ። ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘው ሃብት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት ያለው ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ የቱሪስት ፍሰቱን እንዳልቀነሰው ተናግረዋል። በህዳር ወር ብቻ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ከ17 ሺህ በላይ የውጭ ቱሪስቶች መጎብኘታቸው ጠቅሰዋል። ቱሪስቶችን ማዋከብ፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው አስጎብኝዎች መበራከትና የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር መላላት የዘርፉ ፈተናዎች መሆናቸውን አመልክተዋል። "ችግሮቹን ለመፍታት እንዲቀረፉም ለአስጎብኝ ማህበራት፣ ለሆቴል ባለቤቶችና ለአጋር አካላት በተደጋጋሚ ቢሮው ስልጠና እየሰጠ ይገኛል " ብለዋል። ፈቃድ ሳይኖራቸው በአስጎብኝ ስም ተሰማርተው ቱሪስቱን የሚያውኩ አካላትን ስርዓት ለማስያዝም ቢሮው በየደረጃው ከሚገኙ የሰላምና ደህንነት አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። "በከተማዋ ከ100 የሚበልጡ ህገ ወጥ አስጎብኚዎች በመኖራቸው ቱሪስቶች ላልተገባ ክፍያና እንግልት እየተዳረገ ነው" ያለው ደግሞ የባህር ዳርና አካባቢው አስጎብኝዎች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ማስተዋል ዘለቀ ነው። ማህበራቸው ከሀገር አቀፍ አስጎብኚዎች ጋር በመሆን ቱሪስቶችን ተቀብሎ የማስተናገድ ተግብራትን እያከናወነ መሆኑንም ተናግሯል። የእንግዶችን ማዋከብና  ወጥ እንቅስቃሴ ለማስቆምም ማህበራቸው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እየሰራ እንደሚገኝም አስረድቷል። የዩኒሰን ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ አክሊሉ በበኩላቸው በቅርቡ ወደ ስራ በገባው ባለአራት ኮከብ ደረጃ  ሆቴል ቱሪስቶችን የሚመጥን አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። ወደ ከተማዋ የሚመጡ የውጭ  ቱሪስቶች ቁጥርም እያደገ መምጣቱንና ከዚህም የተሻለ ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል። በውይይት መድረኩ አስጎብኚዎች፣ የፀጥታ አካላት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሆቴል ባለቤቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም