ምጣኔ ሀብቱ በምሁራኑ ዓይን ሲመዘን!

106
ምጣኔ ሀብቱ በምሁራኑ ዓይን ሲመዘን! በአየለ ያረጋል የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት የብዙ ተቋማትና ባለሙያዎችን ቀልብ መሳቡ እሙን ነው። ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ በመንግስት ሪፖርትም ሆነ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋምና ዓለም ባንክ አድናቆት ተቸሮታል። ስሟም በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እያደጉ ካሉ አገሮች ተርታ ተጽፏል። ከዚህ በላይ “ኢትዮጵያ የአፍሪካዋ ቻይና፤ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ትሆናለች’’ የሚል ትንበያም ይፋ አድርገዋል፤ በርካታ መገናኛ ብዙኃንም ይህንኑ ኃይለ ሃሳብ ተጠቅመው ዘግበዋል። ዶክተር አጥላው አለሙ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ምጣኔ ሀብት መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ናቸው። በተመሳሳይ ዶክተር ካሳ ተሻገር በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማትና ሥራ አመራር ኮሌጅ አስተማሪ ናቸው። ምሁራኑ(ዶክተር አጥላውና ዶክተር ተሻገር) ከተቋማቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚያወጣቸውን ትንበያዎች በተመለከተ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ቀጣይነት ላይ አስተያየታቸውን ይናገራሉ። ዶክተር አጥላው የአንድን አገር ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት በሁለት መነጸር ይመለከቱታል፤ ዘላቂና ጊዜያዊ በማለት። “ዘላቂ ዕድገት ሲባል”  ይላሉ “ዘላቂ ዕድገት ማለት ኢኮኖሚው ራሱን በራሱ በውስጥ ሃይሉ እያጠናከረ የሚሄድ ነው። እርስ በርስ የግብዓትና ውጤት ሰንሰለት ራሱን በራሱ እያጠናከረ ከሄደ ኢኮኖሚው ዘላቂ ዕድገት ሊኖረው ይችላል”ይላሉ። በሌላ በኩል ጊዜያዊ ዕድገትን ሲገልጹት “ለአጭር ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ለጊዜው ወይም በአንዳንድ አጋጣሚዎች የመጣ ዕድገት ነው”ይሉታል። ዘላቂ ዕድገት “ትስስሩ የበዛ ነው” የሚሉት ዶክተር አጥላው “ ነገር ግን ኢንዱስትሪው በተለይ የማኑፋክቸሪንግ ከግብርናው፤ ኢንዱስትሪው ከአገልግሎቱ በደንብ የተሳሰረ ነው” ብለዋል። ዘላቂ ዕድገት ለማምጣት ኢንዱስትሪው በተለይም ማኑፋክቸሪንግ ከግብርናው፤ ማኑፋክቸሪንግ ከአገልግሎቱ በደንብ የተናኙ መሆን አለባቸው። ለምሳሌ ማኑፋክቸሪንጉ ከግብርናው ወስዶ በግብርና ላይ የተመሰረተ ከሆነ፤ አገልግሎቱ ደግሞ ከዚሁ ከማኑፋክቸሪንግ በሚወጡ ምርቶች ላይ የተመሰረተ ከሆነ፤ ያለ በለዚያ በአገር ውስጥ የተመሰረተ ከሆነ ይሄ ለዘላቂነት ብዙ እድል አለው። ለምን እርስ በርሱ እየተጋገዘ ይሄዳል ማለት ነው” ይላሉ። “ነገር ግን” ይላሉ ዶክተር አጥላው፤ “ነገር ግን አንዳንድ ኢኮኖሚዎች የኛንም ጨምሮ ህብረተሰቡ የሚጠቀምበት አብዛኛው የማኑፋክቸሪንግ ምርት የሚመጣው ከውጭ ነው። የአገር ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ በአገር ውስጥ በሚገኝ ግብዓት ላይ በብዛት የተመሰረተ አይደለም። ስለዚህ ከውጭ ገዝተን ዕቃ እናስገባና እሷኑ ሰርተን ቢቻል ወደ ውጭ ካልሆነ ከዚሁ አሻሽለን ካልሄድን ለዘላቂ ዕድገት የሚበጅ አይደለም”። ለጊዜው ያለውን የአንድን አገር ዕድገት በማየት ሰዎቹ ሊያደንቁት ቢችሉም፤ ዳሩ ኢኮኖሚው መሰረት አለው ወይ? በራሱ ግብዓት ላይ ነው የተመሰረተው? የሚሸጠውስ ለአገር ውስጥም ነው ወይ? የገበያ እጥረት የለበትም ወይ? መሰል ጥያቄዎች መጠየቅ እንዳለባቸው ነው የሚያብራሩት። ዶክተር ካሳ ኢትዮጵያ በባቡር፣ በኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ በመሳሰሉ ከአረንጓዴ የልማት ዕቅዷ ጋር የሚጣጣሙ ፕሮጀክቶችን እያከናወነች መሆኗ መልካም ገጽታ ሰጥቷታል ባይ ናቸው። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ ወደ ጎረቤት አገሮች የኃይል መስመሮች ዝርጋታ፣ ባሕር አልባዋን አገር ወደ ወደብ የሚያደርሰው የኢትዮ - ጂቡቲ ባቡር ፕሮጀክቶች ለአብነት ያነሳሉ። በአብዛኛው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ “በግንባታ ዘርፍ አልያም በግብርናው ላይ የተንጠለጠለ ነው” የሚሉት ዶክተር ካሳ፤ ከቀጣይነቱ አኳያ ለወደፊት ሊገጥም የሚችለው ጉዳይ አይታወቅም ባይ ናቸው። ምናልባትም ወደፊት በመፍትሔነት ተይዞ እየተሰራበት ያለ የኢንዱስትሪ ፓርክ ቢኖርም፤ እስካሁን ያለው በማምረቻው ዘርፍ ላይ ትኩረት አናሳ እንደሆነ ይገልጻሉ። እናም በምሁራኑ ዕይታ አሁን ላይ የሚታየው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ማምረቻው ዘርፍ ባለመሸጋገሩ ወይም በግብርናው ላይ የተመሰረተ ስለሆነ የተቋማቱ ትንበያ ጥርጣሬ ላይ የሚጥል እንደሆነ ነው የሚገልጹት። በሰው ኃይልና ለወደፊቱ ስኬታማ በሚያደርጉ ዘርፎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ብዙ የቤት ስራዎች ካልተሰሩ ዘላቂነት እንደማይኖረው ዶክተር ካሳ ያወሳሉ። አገሪቷ በተፈጥሮ ዕምቅ ሀብቷና በሰው ጉልበት ትልቅ አቅም እንዳላት የሚናገሩት ዶክተር ካሳ፤ አስፈላጊ የቤት ስራዎች ከተከናወኑ “ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቻይና ትሆናለች የሚለውን፣ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ትሆናለች የሚለው ህልም የማይሳካበት ሁኔታ የለም” ብለዋል። አንዱ የዘርፉ ትልቅ ችግር የነበረው መሰረተ ልማት፣ ጥሬ ዕቃና የተለያየ የመስሪያ ቦታ ማግኘት እንደነበር አንስተው፤ በዚህ ዘርፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለባለሀብቶች መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ነው ያብራሩት። በምጣኔ ሀብት ጽንሰ ሐሳብ መታለፍ ያለባቸው አራት ቁልፍ ጉዳዮች (ትራፕስ) ይጠቅሳሉ። እነሱም “ግጭት፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥገኝነት(ለምሳሌ ነዳጅ አምራች አገሮች)፣ መልካም አስተዳደር እጦትና ወደብ አልባነት/ላንድ ሎክድ/ መሆን ነው። ከነዚህ ውስጥ መውጣት ይገባል” ይላሉ። ከነዚሀ መካከል ሶሰቱ ማለትም ግጭት፣ ወደብ አልባነትና መልካም አስተዳደር (በተለይም የሎጀስቲክስ ጥያቄ) በእኛ አገር መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። ከግብርናም አልወጣችም፤ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ትልቁን ድርሻ አልተሰጠውም። “ለአፍሪካ ማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ትሆናለች የሚለው በመሬት ላይ እንዳይቀር እፈራለሁ” የሚሉት ዶክተር አጥላው፤ እርካሽ የሰው ጉልበትን በብልሀት መጠቅም ከተቻለ፤ ኢኮኖሚው ከተሳሰረ፤ በውጭ ግብይት ብዙ ዘርፎች ከተቀላቀሉና ሌሎች ሃሳቦች በተግባር ከተደገፉ ተስፋው የጨለማ እንዳልሆነ ተናግረዋል። አገልግሎቱ ዘርፍ ልጓም፤ ማምረቻው ፍጥነት ያስፈልገዋል! ዶክተር አጥላው፤ “የኢትዮጵያን አሁን ስናየው ማኑፋክቸሪንጉ ከግብርና ጋር በደንብ የተያያዘ አይደለም። አገልግሎቱ በጣም ትልቅ ነው። ግብርናውን እየተካ ያለው ማኑፋክቸሪንጉ ሳይሆን አገልግሎቱ ነው። ሌሎች ትልቅ ዕድገት ላይ የደረሱ አገሮች በታሪክ እንደምናየው ግብርናውን መጀመሪያ የወሰደው ኢንዱስትሪው ነው” ይላሉ።  አገልግሎቱ “ኢንዱስትሪውን ተከትሎ የሚያድግ ዘርፍ ነው” የሚሉት ዶክተሩ፤ በአደጉ አገሮች  አገልግሎቱ ያደገውም በዚህ ዑደት መሆኑን ያስረዳሉ። በኢትዮጵያ ግን ሳናድግ አገልግሎቱ መቆለሉን ነው የተናገሩት። ማምረቻው ተወስኖ አገልግሎቱ መቆለሉ ደግሞ ለዘላቂ ዕድገት እንደማይበጅ ነው ያብራሩት። “ማኑፋክቸሪንግ ገና ነው። በአገሪቷ ውስጥ ኮ አምስት በመቶ ነው። የገቢ ንግድ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ ማየት ነው። አብዛኛው የገቢ ንግድ የሚደረገው ማኑፋክቸሪንጉ ነው። ይሄ መተካት አለበት። ገና ብዙ ሰንሰለት ሳናበጅ ብዙ መናገር አንችልም። ዘላቂ ዕድገት ነው ብሎ ለመናገር ገና ነው”። “የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ድርሻ አናሳ ነው” የሚሉት ዶክተር ካሳ፤ “ለምሳሌ የተለያዩ አገሮችን ብታወዳድር በተመሳሳይ ደረጃ የነበሩ በ1980ዎቹ ሽግግሩን ስታይ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ተሸጋግረዋል፤ ተመሳሳይ አቀራረብ የሚከተሉ አገሮች አሉ። ነገር ግን የኛ ግን በጣም ቀርፋፋ ነው። የኢንዱስትሪ እድገቱ ማለት ነው፣ በተለይም ማኑፋክቸሪንግ። ምክንያቱም ከ30 በመቶ በላይ ሼሩ ኮንስትራክሽን ላይ ስለሆነ ያን ስታይ በጣም ብዙ መሰራት አለበት። በጣም ብዙ ይቀረናል” በማለት ያብራራሉ። አክለውም በአጠቃላይ የተሻለ ኢንቨስትመንትም መሳብ የተቻለበትን ዕድል በብልሃት መጠቀም ይገባል። ዶክተር አጥላው “አገልግሎቱ ከሚገባው በላይ አድጓል። ሰው ለምን ወደ አገልግሎቱ ምርጫውን ያደርጋል፤ በአንጻራዊነት ወደ ማኑፋክቸሪንግ መግባት አደገኛና አስቸጋሪ እየሆነ ነው እኛ አገር” በማለት ምክንያቱን ያብራራሉ። “ማኑፋክቸሪንግ ዕውቀት ይፈልጋል፤ ዕውቀት ያላቸው ሰዎችን መሰብሰብ ይፈልጋል፤ ሁለተኛ ትልቅ ዕቅድ ይፈልጋል፤ ስራው አዋጭነት ጥናት ይፈልጋል፤ ለመሳሪዎች ካፒታል ይፈልጋል፤ ምቹ ስፍራ፣ ቤት፣ መስሪያ ቦታ፣ (ለማምረቻና ለመጋዘን)፤ መሰረት ልማት (መንገድ፣ ኤሌክትሪክ፣ ውሃ፣ ስልክ) ይፈልጋል። እነዚህን ማግኘት ከባድ ነው እኛ አገር፤ ንግድ ቢሆን ኑሮ ግን አንድ መጋዘን ሰርቶ ይጨርሳል” ይላሉ። የኢንዱስትሪ ትልቅ ዕቅድ፣ ከፍተኛ ወጭ ያለው ማሽነሪና ብድር እንደሚፈልግ አጽንኦት ይሰጣሉ። “ከዚህም በላይ እንዴትና የት እሸጠዋለሁ ማለት ያስፈልጋል፤ ከተመረተ በኋላ ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች ጋር ተወዳድሮ ነው የሚያሸንፈው፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ልወድቅ እችላለሁ ብሎ ነው የሚፈራው” ሲሉ ነው የባለሀብቱን ስጋት የገለጹት። ለዚህ ስጋት የዳረገው ደግሞ በጽሁፍ፣ በስትራቴጂ፣ በዕቅድ ደረጃ እንጂ ተግባራዊ ድጋፍ ባለመኖሩ እንደሆነ ይገልጻሉ። ማኑፋክቸሪንጉን ለመደገፍ የሊዝ ፋይናንስ ለማቅረብ በሚወራበት አገር እንዴት በማምረቻው ዘርፍ ተዋናዮች ቸላ አሉት በሚለው ላይም ዕይታቸውን ይገልጻሉ። “ባንኮቹን የሆነ መያዣ ነገር ከሌለ ከትምህርት ቤት በኢንጂነሪንግ ወይም በሙያ ቴክኒክ ተመርቆ ዝም ብሎ የሚያገኝበት ሁኔታ ያለ አይመስለኝም። ተመራቂዎች ደግሞ ባንኮች የሚያወጧቸውን መስፈርቶች ማሟላት አይችሉም። ቢያሟሉም የተለያዩ እንቅፋቶች አሉበት። ይህ ነው ብሎ ለመናገር ጥናት ቢያስፈልገውም ብዙ ህዝብ ያለበት አገር፣ ብዙ ሥራ ፈት/አጥ/ ያለበት አገር፣ ለመስራት እንፈልጋለን በሚሉበት አገር፣ ብዙ ወጣት ባለበት አገር፣ በምህንድስናውም በቴክኒክና ሙያ ትምህርትም የሚመረቁ ብዙ ሰዎች ባሉበት አገር፤ ትንሽም ብትሆን ሀብት ኑሯቸው ለመስራት በሚፈልጉበት አገር ለምንድን ነው ማኑፋክቸሪንግ ላይ ሰው የሚጠፋው? ይህ የሚያሳየው ወደ ዘርፉ ሰው የማይገባው እንቅፋት መኖሩን ነው። እንቅፋቱን ፈልጎ ማግኘት የመንግስት ሃላፊነት ነው። መንግስት ሄዶ ማምረቻ ፋብሪካ ማቋቋም ሳይሆን ችግሮችን መፍታት ነው። በኢንጂነሪግ ወይም በቴክኒክና ሙያ ትምህርት  የተማረው ሰው ተግባራዊ ትምህርት አልተማረም ምናምን ሊባል ይችላል፤ ነገር ግን ሁሉም ተቀጥሮ ለመስራት የሚያስቸግር ሰው አይደለም። ሁልጊዜም ስራ ፈጣሪዎች ጥቂት ናቸው በማህበረሰቡ ውስጥ። ግን አንድ ኢንተርፕርነር በአካባቢው ሺዎችን ይይዛል። ጥቂት ኢንተርፕረነሮች እንኳን ማሳደግ ብንችል ይበቃል። ሁሉም ፈጣሪ አይሆንም በህብረተሰብ ውስጥ ተፈጥራዊ ነው። እነርሱን ተሽቀዳድሞ መደገፍ ነው፤ እነርሱን ከቀጨሃቸው ግን ችግር ነው” ይላሉ። ምሁራኑ በአገር ውስጥ ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ምርትና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ተሳትፎም መፈተሽ ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ያምናሉ። በኢንዱስትሪ ፓርኮች በአብዛኛው ልብስና ጨርቃ ጨርቅ መሆኑን ይናገራሉ። ነገር ግን ሌሎች መስኮችም መካተት እንዳለባቸው ያብራራሉ። ጥሬ ዕቃውም ከአገር ውስጥ የሚቀርብበት አማራጭ መቅረብ እንዳለበት ባለሙያዎች ይናገራሉ። “ባለሀብቶች ምን ፍለጋ ነው የሚመጡት? የኛን ሰው አሰልጥነው በኛው ሰው ተጠቅመው፤ እኛ ራሳችን ለማምረት እንድንችል ደረጃ ላይ ለመድረስ ካልሆነ፤ ለምሳሌ ቻይናዎች የሚጠቀሙት እንደዚህ ነበር፤ ቻይኖች የራሳቸው ዜጎች እንዲሰሩ እያደረጉ ነበር የሚሰሩት እንጂ ዝም ብሎ የውጭ ኩባንያ መጣ ለራሱ አምርቶ ሸጠ፤ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ አገኘች በሚለው ብቻ አይደለም። የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ብዙም አስተማማኝ አይደለም። ለኢንዱስትሪ ዕድገት ትልቁ ችግር የሆነው ምንድን ነው? “ዕቃዎችን ከውጭ እንደመጡ መጠቀም እንጂ መልሰን እናምርታቸው፣ እንሞክራቸው፣ አፍርሰን እስኪ እንስራቸው የራሳችን ምርት እስኪ እናውጣ” የሚል በመንግስትም በግልም ደረጃ ብዙ አይታየም። እናም ኢትዮጵያ እንደዚያ አይነት አቅም ሳታዘጋጅ ዝም ብሎ ከውጭ መጥቶ አምርቶልኝ ይሄዳል ብለህ እስካሁን ብዙ የያጣናቸው ዕድሎች አሉ” በማለት ዶክተር አጥላው ያብራራሉ። ግንባታን እንደ ምሳሌ የሚያነሱት ባለሙያው፤ የአገር ውስጥ መሃንዲሶችና ተቋራጮች አቅም ማሳደግ እንጂ ሁሉን የውጭ ሰው አምርቶ እንዲሰጠን መፈለግ አዋጭነት የለውም ነው የሚሉት። “ጊዜው መማሪያም ማምረቻም ነው። ለማንም የምንሰጠው አይደለም ይህን ዕድል፤ በርግጥ ከውጭ መማር አለብን። ለምንድነው ይህን ሁሉ መሀንዲስ የምናመርተው፤ ይህን ሁሉ የቴክኒክና ሙያ ባለሙያ የምናመርተው! ዕውቀት እያመረትን ነው፤ መሀንዲስ ስታመርት መሀንዲስ ምን እንዲሰራ ነው የምትፈልገው። ዲዛይን እንዲያደርግ፣ በአገር ውስጥ ጥሬ ሀብት ላይ ተመርኩዞ ዲዛይን አድርጎ ወደ ምርት እንዲያመጣ፣ በአገር ውስጥ ሰርቶ በአገር ውስጥና በውጭ እንዲያቀርብ ነው። ይህ አጣብቂኝ ውስጥ የገባንበትን የውጭ ምንዛሬ ይቀንሳል” በማለትም ያክላሉ። እንደ ኬሚካልና ብረታ ብረት ምርቶችን ማምረት፣ በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን እንዲሰማሩ መወዳዳር እንዲማሩና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። ዶክተር ካሳ በበኩላቸው “ከውጭ የሚመጡ ባለሀብቶች ወደ አገር ውስጥ ሲመጡ ብዙውን ጊዜ ወደ ሪል ስቴት፣ ኮንስትራክሽን፣ እንደዚህ በፍጥነት ጥቅም የሚያስገኝላቸውን እንጂ በዘላቂነት ግብርናን ወደ ኢንዱስትሪ ትራንስፎርም የሚያደርግ ስራ ላይ አይደለም እየተሳተፉ ያሉት። እርሱ ደግሞ ትልቅ ችግር ነው” በማለት ይገልጻሉ። “የምሥራቅ እስያ አገሮች የገቢ ተኪ ምርት ላይ ስኬታማ ነበር” ሲሉ ነው የገለጹት ዶክተር ካሳ። ይህ ደግሞ በአገር ውስጥ መመረት የሚችሉ ምርቶችን ከውጭ ማስገባቱን ከመቀጠል ይልቅ “ዞሮ ዞሮ የሚወድቀው የአገር ኢኮኖሚ ስለሆነ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማሳተፍ ተገቢ ነው” ይላሉ። በርካታ አገሮች ከውጭ ባለሀብቶች ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ላይ አቅደውበት ሰርተው ዕውቀት ማሸጋገራቸውን ይናገራሉ። እኛ ጋር ግን ታቅዶበት እየተሰራ አለመሆኑን ነው ያብራሩት። በኢንዱስትሪ ፓርኮች በአብዛኛው ቴክኒካል ስራውን የውጭ ዜጎች እንደሚያከናውኑት ገልጸው፤ በዚህ መልክ ትራንስፎርም ስለማይደረግ አቅዶ መስራትና አገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማሳደግ፤ የወጪ ንግድ ማስተዋወቅ አስፈላጊ ተግባር መሆኑን አጽንኦት ይሰጣሉ። ግብርናው ቢዘምን ግብርና የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ነው። በኢኮኖሚው የአንበሳ ድርሻ ይዟል። የሽግግሩ መዳረሻ ኢንዱስትሪ ቢሆንም የግብርናው ምርትና ምርታማነቱ ማደግ ይገባዋል። ለኢንዱስትሪው በቂና ጥራት ያለው ጥሬ ዕቃ ማጉረስ አለበት። ከ80 በመቶ በላይ ዜጎች የኢኮኖሚ ምንጭ ነውና ለኑሮና ሕይወታቸው መሻሻል ግብርናውን ማዘመን አንዱ አብይ ጉዳይ ነው። እናም ምሁራኑ ወደፊት ለሚገነቡት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ግብዓትነት ብቻ ሳይሆን ግብርናውን ማዘመን “ለሁሉም የአገሪቷ ዕድገት ዘላቂነት ወሳኝነቱ አሌ የማይባል ሐቅ ነው” ይላሉ። “ግብርናው ለማዘመን አቅም ያለው ገበሬ መፈጠር አለበት” ይላሉ ዶክተር አጥላው። አብዛኛው ገበሬ ከዕጅ ወደ አፍ በሆነ ግብርና ላይ የተሰማራ ነው፤ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው  የኢትዮጵያ ገበሬ ከአንድ ሄክታር በታች ነው የሚያርሰው። ከትንሿ መሬት የሚያመርተው ገቢ ትንሽ ነው፤ ከቀለባቸውና ከራሳቸው በላይ ሊቆጥቡት የሚችሉት ሀብት ማፍራት አይችልም። አንድ ሄክታር ላይ ለዓመት ምግቡ፣ ልብሱ፣ ለመኖሪያው…. አድርጎ የምትተርፈው ምንድን ናት? ይህንን ማዘመን እንዴት ነው የሚቻለው? ሲሉ ይጠይቃሉ። እንደ መፍትሔም ለግብርናው ዘመናዊ ግብዓቶችን(ተፈጥራዊና ሰው ሰራሽ) ሲጠቀም መሆኑን ያነሳሉ። መሬትን ለም ለማድረግ ውሃም ያስፈልጋል። እንደ አገር ታላላቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች፤ ለገበሬው ደግሞ ታናናሽ ፓይፖች፣ ፓምፖች፣ ማሰራጫዎች ያስፈልጋል። መሬት ውሃ እንዲቋጥር የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ይፈልጋል። ገበሬው በሚያመርትበት ጊዜ ዘመናዊ መሳሪዎች መጠቀም ይፈልጋል። ዘመናዊ ማረሻዎች፣ መዝሪያዎች፣ ማረሚያዎች ወይም ኬሚካል ይፈልጋል። ብዙ ዘመናዊ ነገሮች ይፈልጋል። ድህረ ምርት መሰብሰቢያዎች ማጨጃ፣ መውቂያ፣ ምርት ማጠራቀሚያ፣ ማጓጓዣ፤ ማስቀመጫ ይፈልጋል። እነዚህ ሁሉ የኢንዱስትሪ ምርቶች ናቸው፤ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች። ዶክተር አጥላው ፤ “እነዚህ ዘመናዊ ገበሬ ቦት ጫማ፣ ባርኔጣ፣ የፀሀይ መከላከያ ዣንጥላው፤ ከነ ጓንቱ፣ ከነማጭዱ ሁሉም ነገር ዘመናዊ ሲሆን አያያዙም ለምሳሌ በአካባቢው ብክለት እንዳይኖር የሚጠቅምባቸው መሳሪዎች መድሃኒትና ኬሚካሎችን የሚይዝባቸው ብዙ ዘመናዊ ነገሮች አሉ” ይላሉ። ከማዳበሪያ በተጨማሪ ጉልበት የሚቆጥቡ ሜካኒካል ቀሳቁሶችን ገንዘብ ቆጥቦ ለመግዛት ከአንድ ሄክታር መሬት በታች ያለው ገበሬ አቅም እንደሌለው ይናገራሉ። ስለዚህ ያለው ዕድል ሰፋ ያለ መሬት ለማረስ የሚያስችለው ሁኔታ መፍጠር አለበት። በሌላ በኩል በተጣበበ መሬት የተጠራቀመው ገበሬ ለተወሰኑ ሰዎች እየተተወ ከግብርናው መውጣት እንዳለበት ይመክራሉ። “ኢኮኖሚው በራሱ ወደ ከተሞች መሳብ አለበት። ከገጠሩ ወደ ከተማ ስራዎች መምጣት አለበት። ለዚህ ደግሞ ፋብሪካዎች፣ የከተማ ስራዎች መስፋፋት አለባቸው። አንድ ገበሬ ብዙ ሰው የሚጠቀምበትን መሬት ቢጠቀምበት ሜካናይዝድ እርሻ ማድረግ ይችላል። ከዛም የተገኘውን መቆጠብ ይችላል፤ አዳዲስ ግብዓቶች የመግዛት አቅም ይኖረዋል። እንደዚህ ትራንስፎርም ካልሆነ ከአንድ ሄክታር የማትበልጥ መሬት ከነቤተሰቡ ይዞ እርሷን እየበላ አብዛኛው ዓመቱን ቁጭ ብሎ ማሳለፍ የለበትም”። በመሬት ማነስና በጉልበት ብክነት መካከል ስላለው አለመጣጣም እንዲህ ይናገራሉ። “ለምሳሌ አንድ ሄክታር ለማረስ አራት ቀን ነው የሚፈጅበት። አራት  ጊዜ ቢያርሳት 16 ቀን ነው በዓመት ውስጥ፣ 16 ቀን ለማረም፤ ሌላ 16 ቀን ለማጨድ ቢፈጅበት፤ በዓመት 48 ቀናት ናቸው ከነቤተሰቡም ከሰራ። ገበሬ መሬቱ ትንሽ ስለሆነች ጉልበቱ ይባክናል”። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ባለፉት 40 ዓመታት የተከተልነው የግብርና እና የመሬት አጠቃቀም ስትራቴጂ ውጤት እንደሆነ አስተያየታቸውን ይናገራሉ። ገበሬው መሬቱን ለቆ ሲሄድ “እነጠቃለሁ” በሚል ፍርሃት ተዘዋውሮ ለመስራት እንደማይፈልግ ገልጸው፤ አሁን የተጀመረው ‘የይዞታ ማረጋገጫ’ ምናልባት የባለቤትነት መብት ስለሚሰጥ የገበሬውን ስጋት ሊያቃልል እንደሚችል ያብራራሉ። ሲያጠቃልሉም “ ለዘመናዊ ግብርና ዘመናዊ ግብዓት ያስፈልጋል፤ እነዚህ ግብዓቶች ደግሞ በቀላሉ አይገኙም። አንደኛ በአገር ውስጥ መመረት አለባቸው።ሁሉንም ግብዓቶች ከውጭ ለማምጣት ዋጋው ውድ ነው፤ በገበሬው አቅም። ርካሽ አድርገን ማምረት አለብን። ርካሽ የሆነውን የገበሬ ጉልበት ተጠቅሞ ለምን ዘመናዊ ማዳበሪያ አንሰራም። ኬሚስት፣ ኬሚካል ኢንጂነር፣ ግብርና የምናስተምረው ለምንድን ነው! እንዲህ አይነት ነገሮችን እንዲያሻሽሉ ነውና። መጀመሪያ ማኑፋክቸሪንጉ ለአገራችን ግብርና ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ምርቶችን ለማምረት ዝንባሌ ሊኖረው ይገባል። ገበሬው ደግሞ ከግብርና እየወጣ ሌላ ስራ መስራት የሚችልበትን የመቆጠብ አቅም ማጎልበት አለበት” ብለዋል።  ስጋትና ተስፋ- እንደማጠቃለያ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ቀጣይነት “የአገሪቷ ፖለቲካው ቁልፍ ነው” ይላሉ ዶክተር አጥላው። “ስለማኑፋክቸሪንግ እናወራለን፤ ስለግብርናው እናወራለን፤ ፖለቲካው የተረጋጋ ፖለቲካ እስካልሆነ ድረስ፤ ተቀባይነት ያለው ስርዓት እስካልሆነ ድረስ፤ ያ ሁሉ ድካም ከንቱ ነው” በማለት ይገልጻሉ። አንዱ ትልቁ ስጋት የተረጋጋ ፖለቲካ አለመኖር ነው። የፖለቲካ አለመረጋጋት እጅግ በጣም ብዙ ኢኮኖሚያዊ ችግር ያመጣል፤ ዛሬ ሳይሆን በተከታታይ ዓመታት የሚያስከትለው ውጤት ከባድ ነው። ካልሰከነ ሁሉም እምቦጭ ነው፤ በአስተሳሰብም በኢኮኖሚ ላይም። “ኢትዮጵያም ችግሮችን ፈታ በተረጋጋ ሁኔታ ማሰብ አለባት’’ይላሉ። የወጪ ንግድና የውጭ ምንዛሬ ይቀንሳል። የምናገኘውንም የውጭ ምንዛሬ ምን ላይ እናውለው ማለት ይገባል። ይህ የሚሆነው የተረጋጋ ፖለቲካ ሲኖር ነው። በዶክተር ካሳ አባባል ደግሞ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አለማደግ ለአገሪቷ ዕድገት ቀጣይነት አንዱ ስጋት ነው። አገር በቀል አልሚዎች አቅም አለመገንባታቸውም ሌላው ስጋት ነው። እናም ማኑፋክቸሪንግና አገር በቀል አልሚውን መደገፍ ያሻል። የገንዘብ፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ ማበረታቻዎች ያስፈልጋሉ። ወጥ/ኮንሲስተንት/ ፖሊሲ ያስፈልጋል። ትኩረት ተሰጦት ከነበረው ከመንግስት አቀራረብ ወደ ግሉ ዘርፍ መሸጋገር በአንጻራዊነት ተመራጭ ነው። ሁሉን ኢንዱስትሪ ፓርኮች በታቀደላቸው ልክ በፍጥነት ተገንብተው ወደ ስራ ቢገቡ “የተሻለ ነገር ይገኛል” የሚሉት የዶክተር ካሳ ሃሳቦች ናቸው። በሌላ በኩል ትልቁ ስጋት ሙስና ነው ይላሉ ምሁራኑ። በመሬት አስተዳደር፣ በምርት አስመጭና ላኪው የሚፈጸሙ የሙስና ተግባራት ካልተወገዱ ችግር ነው። የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የባንክ ፋይናንስ አቅርቦት፣ የታክስ ስርዓቱ ካልተስተካከለ ኢኮኖሚው ወደፊት አይራመድም። ምሁራኑ ለኢዜአ አስተያይታቸውን ከሰጡ በኋላ በቅርቡ መንግስት ታላላቅ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ባለሀብቱ ለማዞር መወሰኑ ይታወቃል። ከሁለት ወራት በፊት መንበረ ስልጣናቸውን የተቆጣጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶክተር) በአገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካ መስክ ብሩህ ተስፋ ፈንጥቀዋል። አገሪቷ ለገጠማት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በመቀልበስ ሕዝቦች ወደ አንድነት እንዲመጡ በተለያዩ መስኮች በርካታ ዕርምጃዎችን ወስደዋል። በብዙኃኑ ዘንድም ድጋፍና ይሁንታን ተቀብለዋል። ምናልባት ፖለቲካዊ ትኩሳቶች ከተፈወሱ ምሁራኑ እንዳሉት ወደፊት ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችም ተስፋ ይኖራቸው ይሆን?          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም