በድሬዳዋ ክረምትን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል ሥራ እየተሰራ ነው

89
ድሬዳዋ ሰኔ 16/2010 በድሬዳዋ አስተዳደር ክረምትን ተከትሎ የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑን የአስተዳደሩ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አርጋው ተናገሩ። ሕብረተሰቡ የግልና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ ወባ፣ ደንጊና አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታዎችን የመከላከል ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጤና ቢሮ አሳስቧል፡፡ የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አርጋው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ የክረምት መግባትን ተከትሎ በድሬዳዋ ለብዙ ነዋሪዎች ሕመምና ስቃይ ምክንያት የሚሆኑ ተላላፊ በሽታዎች ይከሰታሉ። በተለይ በትንኝ አማካኝነት አምራች ኃይሉን ጭምር ለሕመም በመዳረግ ሕብረተሰቡን ለተለያየ ጉዳት የሚዳርጉ የደንጊና የወባ እንዲሁም የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ሕመሞች ዋንኞች ተላላፊ በሽታዎች መሆናቸውን ነው ዶክተር ሙሉቀን የገለፁት፡፡ በሽታዎቹን አስቀድሞ ለመከላከል የሚመለከታቸው ሴክተሮች በሙሉ የተካተቱበት ኮሚቴ ተዋቅሮ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።  በእዚህም የወባ መከላከያ አጎበር የማሰራጨት፣ ፀረ ወባ ኬሚካል በትንኝ መራቢያ ቦታዎች ላይ የመርጨትና ከፌደራል ጤና ጥበቃ ጋር በመሆን አስፈላጊውን የመድኃኒትና የቁሳቁስ ግብአት የማሟላት ሥራዎች ተሰርተዋል። ከእዚህ በተጨማሪ የጤና ጣቢያዎችና የጤና ኬላዎች አስፈላጊውን ዝግጅት ከማድረግ ባለፈ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ሕብረተሰቡን ቤት ለቤት በመሄድ በማስተማር ንፅህናው የተጠበቀ አካባቢ እንዲፈጠር በማድረግ ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡ ዶክተር ሙሉቀን እንዳሉት የተላላፊ በሽታዎችን የመከላከልና የመቆጣጠሩ ሥራዎች ውጤታማ የሚሆኑት ሕብረተሰቡ ሁል ጊዜ የራሱንና የአካባቢውን ንጽህና ሲጠብቅና ራሱን ከበሽታዎች ሲከላከል ነው፡፡ በጤና ጥበቃ ቢሮ የድንገተኛ አደጋዎች ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ዳንኤል ተሾመ በበኩላቸው ወባና ደንጊ በሽታዎችን የሚያስተላልፉት ትንኞች የተለያዩ ቢሆኑም የሕመሞቹ ምልክቶች ተቀራራቢነት እንዳላቸው ገልጸዋል። "መቆረጣጠም፣ ራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለትና መሰል ሕመሞች የበሽታዎቹ ምልክቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሕብረተሰቡ ምልክቶቹን ሲያይ በአፋጣኝ ወደ ጤና ጣቢያ መሄድ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ በድሬዳዋ ገጠርና ከተማ ዘንድሮ 169 ሰው በወባ፣ 163 ሰው በደንጊ 328 ሰዎች ደግሞ በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታዎች ታመው ተገቢ ሕክምና አግኝተው ጤናቸው መመለሱን አቶ ዳንኤል አስታውሰዋል፡፡ በድሬዳዋ የህዝብ ቁጥር በብዛት በሚገኝበትና ተላላፊ በሽታዎች መከሸቻ በሆነው የሳቢያን ቀበሌ የጤና ማስተባበሪያ ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ትዕግስት አበራ ውሃ ያቆሩ አካባቢዎችን በማፋሰስና በማድረቅ፣ የተዘጉ የውሃ መፍሰሻዎችን በመክፈት፣ የቆሸሹና ለትንኝ መራቢያ የሆኑትን ስፍራዎችን በማድረቅ በሽታዎቹን የመከላከሉ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በተጨማሪም ለተላላፊ በሽታዎች መንስኤ በሚሆኑ ስፍራዎች ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች ተገቢውን ትምህርት መሰጠቱንም ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ ከተማ ጤና ጣቢያ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ሲስተር ሕይወት ሙሉ በበኩላቸው ሕብረተሰቡን ስለተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በማስተማርና ችግር ያለባቸውን ወደ ሕክምና በመውሰድ ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል። ቤት ለቤት በመዘዋወር ሕብረተሰቡ የራሱንና የአካባቢውን ንጽህና በተገቢው መንገድ እንዲጠብቅ በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም