ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን የዞን አምስት ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ልታዘጋጅ ነው

636

ኢዜአ ታህሳስ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን የዞን አምስት ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና እንደምታዘጋጅ ፌዴሬሽኑ አስታወቀ።

የአፍሪካ ዞን አምስት ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ሂሻም ኢልሃረሪ በኢትዮጵያ ጉብኘት አድርገዋል።
የጉብኝታቸው ዓላማም በኢትዮጵያ ያለውን የቅርጫት ኳስ ስፖርትና ውድድር የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ  ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር ለመነጋገር ነው።

የኢትዮጵያ ቅርጯት ኳስ ፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይመር ሃይሌ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የቅርጫት ኳስ ስፖርትን ማሳደግ ይቻል ዘንድ በዘርፉ ስልጠናዎች በሚዘጋጁበት መንገድ ላይ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ውይይት ተደርጓል።

በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት እድሜቸው ከ16  ወይም ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች የሚካፈሉበት የዞን አምስት ቅርጫት ኳስ ውድድር ማስተናገድ እንደምትችል የአፍሪካ ዞን አምስት ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አረጋግጠዋል።

ለውድድሩ ውጤታማነት ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶችን ማሟላት እንዳለባትም ተጠቁሟል።

ውድድሩ የሚካሄድበት ወቅት ወደፊት የሚወሰን መሆኑም ተመልክቷል።

የአፍሪካ ዞን አምስት ቅርጫት ኳስ ኢትዮጵያን፣ ግብፅ፣ ሱዳንን፣ ኡጋንዳን፣ ኤርትራን፣ ብሩንዲንና ሶማሊያን ጨምሮ 11 አገራትን ያሳትፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢንጂኒየር ሂሻም አልሀሪሪ በአዲስ አበባ ቆይታቸው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚንና የኢትዮጵያ ብሄራዋ ሙዚየምን ጎብኝተዋል።

በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በነበራቻው ቆይታም የኢትዮጵያ መንግስት ለስፖርቱ ትኩርት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።