ጥምቀት በዓለም አቀፍ ቅርስነት መመዝገቡ ቱሪዝምን በማነቃቃት ገቢን ያሳድጋል

142

ኢዜአ፤ ታህሳስ/ 2012 በዩኔስኮ በዓለም የማይዳሰሱ ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በዓል የአገሪቱን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በማነቃቃት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ እንደሚያሳድገው የጎንደር ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳዳሪ ተናገሩ፡፡ አስተዳዳሪው አቶ ጌታሁን ስዩም ለኢዜአ እንዳሉት በጎንደር ከተማ በየዓመቱ በወርሃ ጥር በታላቅ ሃይማኖታዊ ስርአትና ባህላዊ ክዋኔ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ለከተማው ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ነው፡፡

የከተማው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ 60 በመቶ የተመሰረተው በቱሪዝም ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ የጥምቀት በዓልም ከሃይማኖታዊ ስርአቱ ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን አስረድተዋል።

የጥምቀት በዓል አከባበርን ለመመልከት በየዓመቱ በርካታ የውጪ አገር ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡና አሁን ላይ ደግሞ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ የውጭ ቱሪስቶችን የበለጠ እንደሚስብ አመልክተዋል።

ይህም ከከተማዋ ባለፈ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቶችዋን ለዓለም ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥርና አለም አቀፍ እውቅና የሚያስገኝ መሆኑንም አቶ ጌታሁን ተናግረዋል፡፡

እንደእሳቸው ገለጻ ጥምቀት በዓለም አቀፍ ቅርስነት መመዝገቡ ሃይማኖታዊ በዓሉን ጠብቆና ተንከባክቦ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

"የፋሲል ቤተ-መንግስትን የሚጎበኙ የውጪ አገር ቱሪስቶች ፍሰት እየጨመረ መጥቷል" ያሉት አቶ ጌታሁን በህዳር ወር ብቻ ከ5 ሺህ በላይ የውጪ አገር ቱሪስቶች እንደጎበኙት ተናግረዋል፡፡

ቱሪዝሙ ለከተማው ስራእጥ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በፋሲል ቤተ-መንግስት ብቻ ከ100 በላይ ቱሪስት አስጎብኚ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ለቱሪስቶች መኪና በማከራየት፣ ምግብ በማብሰልና ፎቶ በማንሳት የተሰማሩ በርካታ ወጣቶች የስራ እድል ፈጥሯል። የከተማው የቱሪስት ፍሰት ከጥምቀት ዋዜማ ጀምሮም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡

"የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ዘንድሮ በዓሉን በልዩ ሁኔታ በጎንደር ከተማ  ለማክበር እድል ፈጥሯል" ያሉት ደግሞ የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ጥሩነህ ናቸው፡፡

በዓሉ የጎንደር ልዩ መለያ እስከመሆን መድረሱን ከንቲባው ጠቁመው በከተማዋ እንግዶችን ለመቀበል ከምንግዜውም በተለየ ዝግጅት እየደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓሉ የሰላምና የአብሮነት መገለጫ በመሆኑ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርአቱን በጠበቀ መንገድ በየዓመቱ በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር ከተማ አስተዳዳሩ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡ 9 ታላላቅ ቅርሶች እንዳሏት የገለጹት ደግሞ የፌደራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ናቸው፡፡

"ቅርሶች ዓለም አቀፍ እውቅና ሲያገኙ ቅርሶችን የመጠበቅና የመንከባከብ ከባድ ኃላፊት የዓለም ህብረተሰብ የጣለብን መሆን መገንዘብ ይገባል" ብለዋል፡፡

እነዚህን ዓለም አቀፍ ቅርሶችን ከጉዳትና ከጥፋት ጠብቆ በማቆየት የውጭ ቱሪስቶች ወደኢትዮጵያ እንዲጎርፉና የስራ አድል እንዲፈጥሩ ለማድረግ አጋጣሚውን መጠቀም ተገቢ መሆኑንም አሳስበዋል፡

   በተመሳሳይ ዜና የጥምቀት በዓል ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመር ከዘርፉ የሚኖረውን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ የሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል።

በመምሪያው የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ ጥላሁን አባተ ለኢዜአ እንዳሉት ጥምቀት የዓለም የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ በአገር ገጽታ ላይ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

ይህም ወደኢትዮያ የሚመጡ የቱሪስቶችን ቁጥር በመጨመርና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ ኢኮኖሚ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ከአገራዊ ፋይዳው በተጨማሪም ዜጎች የባህል ልብሶችን፣ የእደ ጥበብ ውጤቶችን፣ የሥጦታ እቃዎችንና ሌሎች ምርቶችን ለቱሪስቶች በማቅረብና በአስጎብኚነት በመሳማራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

በመጪው ጥር 11 ቀን የሚከበረውን የጥምቀት በዓል በላል ይበላ እና በሌሎች የዞኑ አካባቢዎች በድምቀት ለማክበር የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም አቶ ጥላሁን አመልክተዋል።

በገና በዓል በላል ይበላ ቤተማርያም ቤተክርስቲያን ሚካሄደው "የቤዛኩሉ" ሃይማኖታዊ ክዋኔንም በተመሳሳይ በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ አስፈላጊ መረጃዎችን በማሟላት ለዩኔስኮ መላኩንና መልስ እየተጠበቀ መሆኑን የመምሪያውን መረጃ ዋቢ አድርጎ የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም