ETRSS-1' ሳተላይት የሙከራ መረጃ ልውውጧን አጠናቃ ከቀናት በኋላ የተልዕኮ ስራዋን ትጀምራለች

67
ኢዜአ ታህሳስ 13/2012፡ ኢትዮጵያ ያመጠቀቻት 'ETRSS-1' ሳተላይት የሙከራ መረጃ ልውውጧን አጠናቃ ከቀናት በኋላ ወደ ተልዕኮ ስራ እንደምትሸጋገር የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ሳተላይቷ በቀን አስራ አራት ጊዜ መሬትን የምትዞር ሲሆን፤ እስካሁን ባለው ሂደትም በየእለቱ አራት ጊዜ መረጃ ወደ እንጦጦ ኦብዘራቫቶሪ ማዕከል ትልካለች ነው የተባለው። የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ እስካሁን ባለው ሂደት ከሳተላይቷ ጋር የተሳካ የሙከራ መረጃ ልውውጥ እየተከናወነ ነው። መረጃውም በዋናነት የሳተላይቷን አሁናዊ ሁኔታ የተመለከተ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል። ሳተላይቷ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከማዕከሉ እንድተገብር የሚሰጣትን ተልዕኮ ማከናወን ትጀምራለች ብለዋል። በዋናነትም ግብርናና የተፈጥሮ እንክብካቤ እንዲሁም የአየር ንብረት ሁኔታን በተመለከተ መረጃዎችን መላክ የምትጀምር ይሆናልም ነው ያሉት። ኢንስቲትዩቱ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀትም ተተኪ የስፔስ ሳይንስ ባለሙያዎችን ለመፍጠር እንደሚሰራም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በቀጣይ ሶስት ዓመታትም የኮሙኒኬሽንና ፈጣን የመሬት ምልከታ ሳተላይት(high remot sensetive) ለማምጠቅ እንዲሁም የሳተላይት  ማምረቻና መገጣጠሚያ ጣቢያ ለመክፈት እቅድ መያዙንም አውስተዋል። የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሳተላይት 'ETRSS-1' ቻይና ከሚገኝ ማምጠቂያ ማዕከል ነው ዓርብ ማለዳው ላይ ወደ ህዋ የመጠቀችው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም