የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ስርጭት ለመግታት ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

63
ኢዜአ ታህሳስ 12 ቀን 2012 በአገሪቱ እያንሰራራ ያለውን የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ስርጭት ለመግታት ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አስገነዘቡ። አገር አቀፍ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን ዛሬ በሰመራ ከተማ ተከብሯል ። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትና የአገር አቀፍ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሳህለወርቅ ዘውዴ በአከባበር ስነ ስርአቱ ላይ እንደገለጹት በአገሪቱ በሽታው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ለ15 ዓመታት ሰፊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል። ከዚያ ወዲህ ባሉ ዓመታት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተሰጥቶ በነበረው ትኩረት የቫይረሱ ስርጭት ቀንሶ እንደነበረም አስታውሰዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአመራሩ እስከ ህብረተሰቡ ድረስ በተፈጠረ መዘናጋት የበሽታው ስርጭት ዳግም እያንሰራራ መሆኑን አመልክተዋል ። "የመዘናጋቱ ሁኔታ በእዚሁ ከቀጠለ በሽታው ከዚህ ቀደም ያስከተለው አስከፊ ሁኔታ የማይደገምበት ምንም ዋስትና የለም ያሉት ፕሬዚዳንቷ ፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፉ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል። ችግሩ የሁሉም በመሆኑ ከፖለቲካ አመራሩና ከማህበረሰብ መሪዎች ጀምሮ እስከ ቤተሰብ አባላት ቫይረሱን በመግታት ሂደት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው ክልሉ የኢትዮ- ጅቡቲ  መተላለፊያ ኮሪደር መሆኑና የህብረተሰቡ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ላይ የነበረው ዝቅተኛ ግንዛቤ በክልሉ የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል ። የክልሉ መንግስት ከተለያዩ የማህበረሰብ አመራሮችና  ባለድርሻዎች ጋር በመተባባበር ባከናወናቸው የመከላከልና የቁጥጥር  ስራዎች  የቫይረሱ ስርጭት ከነበረበት አስከፊ ደረጃ  ቀንሶ እንደነበረም አስታውሰዋል። "በህብረተሰቡ ውስጥ የተፈጠረው መዘናጋት እንዲሁም ወጣቱ ክፍል በተለያዩ  ሱሶች ውስጥ መውደቁ  ስርጭቱ ዳግም እንዲያንሰራራ ምክንያት ሆናል" ሲሉም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም የክልሉ መንግስት ከአገር ሽማሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመሆን የተጠናከረ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን ለማከናወን አቅጣጫ ማስቀመጡንም አመላክተዋል ። በቀኑ አከባበር ሰነ- ስርአት ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች የተሳተፉ ሲሆን ባለድርሻዎችም የአጋርነት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም