"ዙምባራ" የግጥም መድብል ተመረቀ

189
ኢዜአ ታህሳስ 11/2012፡ “ዙምባራ” የተሰኘ የግጥም መድብል መጽሃፍ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተመርቆ ለንባብ በቃ፡፡ ገጣሚ አቶ አድማሱ ተክሌ በምረቃው ወቅት እንደተናገረው መድብሉ በ87 ገጾች ውስጥ 83 ግጥሞች ይዟል። ግጥሞቹ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ የህይወት ተሞክሮዎቹ ለአንባቢያን ቢቀርብ ልምድ ሊሆን ይችላል በሚል ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ የግጥም መድብሉ “ዙምባራ” የሚለውን ስያሜ ያገኘው ደግሞ ከተገጣጠመ ቅል የሚሠራው የበርታ ብሔረሰብ ባህላዊ የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ ዙምባራ ድምጽ በሚፈጥረው ሃሴት ተመስሎ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያውን ማንም ሰው ይስራው እንጂ በዘፈቀደ ሊጫወተው እንደማይችል የገለጸው ገጣሚው ግጥምም ቃላትን ከመምረጥ ጀምሮ የተደራጀ ሃሳብ እስከ ማዋቅር ያለው ሂደት ከዙምባራ ጋር እንደሚያመሳስለው አብራርቷል፡፡ በክልሉ ገጣሚያን ቢኖሩም ስራቸው በገንዘብ አቅም ችግር ሳይታተምና ለህዝብ ሳይደርስ የቆዩ እአንዳሉም ጠቁሟል፡፡ ጥበብ አፍቃሪን ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ማህበረሰብ ለዘርፉ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የጠየቀው ደራሲው አርአያ ለመሆን ከመጽሃፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በአካባቢው ተደብቀው ለቀሩ ስራዎች ማሳተሚያ እንዲውል እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ መጽሐፉን የመረቁት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ምስክያ አብደላ ህብረተሰቡ ሃገራዊ ለውጡን በእውቀት ለማደገፍ የንባብ ባህሉን ሊያሳድግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓት የተለያዩ የህብረሰተብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም