ዩኒቨርሲቲዎች ለሀገራዊ አንድነት መሰረት መጣያ እንጂ የሰላም እጦት መነሻ መሆን የለባቸውም... አቶ አገኘሁ ተሻገር

90
ኢዜአ ታህሳስ 11 /2012  "ዩኒቨርሲቲዎች ለሁሉም የሚመቹና ለሀገራዊ አንድነት መሰረት መጣያ እንጂ የሰላም እጦት መነሻ መሆን የለባቸውም" ሲሉ የአማራ ክልል ሰላምና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማስቀጠል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት  የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡ የቢሮው  ኃላፊ  በምክክር መድረኩ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲዎች ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ተማሪዎችን ተንከባክበውና ከጥቃት ጠብቀው የሀገር ተረካቢ ዜጋ ማፍራት አለባቸው፡፡ ተማሪዎቹ ከጎጠኝነትና ቡደንተኝነት አስተሳሰብ በመውጣት ለሀገር እድገት ግንባታና ህዝባዊ አንድነት የበኩላቸውን  እንዲወጡ ማስቻል የዩኒቨርሲቲዎች ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማሩን የሚያውኩ ሰራተኞችም ሆነ ተማሪዎች ተለይተው በህግ አግባብ ሊጠየቁ ይገባል። አቶ አገኘሁ እንዳመለከቱት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት መቋረጥና ሁከት መነሻ የሆኑ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ የግድ ነው። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ‹አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ› ፕሮጀክትም ከተቋቋመበት ዓላማ በመነሳት የዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲቀጥል በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው ሰላም መሆን የከተማዋ የልማት እንቅስቃሴ ላይ አወንታዊ ተፅእኖ ያለው በመሆኑ የተቋሙን ሰላም ለመመለስ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው በነበረው አለመረጋጋት የተጠረጠሩ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ ተማሪዎችና አንድ መምህር ጉዳያቸው በሚመለከተው አካል እየተጣራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከከተማው ካሉ የኃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎችና አመራሮችን የያዘ የሰላምና ልማት ምክር ቤት ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። በገንዘብ በመገዛትም ይሁን ሌላ ዓላማ ይዞ በግቢው ውስጥ ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላትን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል፡፡ በውይይቱ  የሃገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች፣ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባላትና ሌሎችም አካላት ተገኝተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም