የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከቤጂንግ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በትብብር ለመስራት ስምምነት ተፈራረመ

96
ኢዜአ ታህሳስ 11 / 2012 የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከቻይናው የቤጂንግ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በትብብር በመስራት በሁለቱ አገራት እና ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ። የመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ስምምነቱን የተፈራረሙት በቻይና በተካሄደው የቤጂንግ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ጉባኤ ላይ ነው። በስምምነቱ መሰረት ሁለቱ ተቋማት የጋራ በሚያደርጓቸውና በሚመለከታቸው ወቅታዊ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ አንኳር ጉዳዮችና ሁነቶች ዙሪያ የዜና ዘገባዎችንና ተያያዥ የሚዲያ ውጤቶችን ይለዋወጣሉ። በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለውን የባህል፣ ትምህርት፣ የከተሞች ልማት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የትብብር ግንኙነትን ማጠናከር ይቻል ዘንድ በዘርፎቹ የአገራቱን ህዝቦች ግንዛቤ ለማሳደግ በየጊዜው የፅሁፍ፣ የምስልና ድምፅ ዘገባዎችን ማዘጋጀትም የስምምነቱ አካል ነው። ይኸው ለሶስት ዓመታት የሚቆየው የትብብር ስምምነት የጋዜጠኞችንና የሚዲያ ተቋማቱን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የልምድ ልውውጥ ጉብኝትንም ያካትታል። መቀመጫውን በቤጂንግ ያደረገው የቤጂንግ ሚዲያ ኔትወርክ ከ20 በላይ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎችን እንደዚሁም የህትመት ሚዲያዎችን የሚያንቀሳቅስ የቻይና ትልቁ የዜና አውታር ነው። “Connectivity, Mutual Learning, and Win-Win Cooperation" በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደውን ፎረም ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውም የቤጂንግ ሚዲያ ኔትወርክ ነው። በቻይና ርእሰ መዲና ቤጂንግ በተካሄደው የዘንድሮው የቤጂንግ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ፎረም ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ12 አገራት የተጋበዙ 14 የሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎችና ከፍተኛ አርታኢያን ተሳትፈዋል። በፎረሙ ላይ ትምህርታቸውን በቻይና የሚከታተሉ የተለያዩ አገራት የሚዲያ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ100 በላይ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ቻይና ከሌሎች አገራት የሚዲያ ተቋማት ጋር ሊኖራት በሚችለው ትብብር ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል። ተሳታፊዎቹ በአገሮቻቸው የሚዲያ ተቋማት መካከል ጠንካራ ግንኙነት በመመስረት ለህዝቦቻቸው ጥቅም በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። ከተሳታፊዎቹ መካከልም ሩሲያ፣ ጃፓን፣ ቱርክ፣ ፓኪስታን፣ ኢራን፣ ኔፓል፣ ዩክሬንና ቪየትና ይገኙበታል።   የቤጂንግ ዓለም አቀፍ ፎረም ተጋባዥ አገራት የልኡካን ቡድን አባላት ከፎረሙ ስብሰባ ቀደም ብሎ የቤጂንግ ሚዲያ ኔትወርክ የሚዲያ ተቋማትን እንቅስቃሴ ጨምሮ በከተማዋ ያሉ የልማት አውታሮችንና የቱሪስት መስህቦችን ጎብኝተዋል። ቤጂንግ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2022 የምታስተናግደውን የክረምት ኦሎምፒክ ዝግጅትንም የልኡካን ቡድኑ አባላት ጎብኝተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም