የልብስ ስፌት ፋብሪካው ከ600 ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ አደረገ

120

ኢዜአ ታህሳስ 11 / 2012 አባይ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር በጎንደር ከተማ ግማሽ ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ገንብቶ ወደ ስራ የገባው የልብስ ስፌት ፋብሪካ ከ600 ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩ ተገለጸ። የልብስ ስፌት ፋብሪካው እንቅስቃሴ  ዛሬ በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተጎብኝቷል።

የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተላይነህ ውብነህ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት ፋብሪካው  በቀን ከ7 ሺህ በላይ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ሦስት አይነት አልባሳትን በማምረት ለሃገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ በሂደት ላይ ይገኛል።

ወደ ስራው የገባውም ከ610 በላይ የልብስ ስፌት ማሽኖች በማሟላት ነው።

ከሚቀጥለው ጀምሮም ጅንስና ካኪ ሱሪዎችን እንዲሁም ቲ-ሸርቶችን ማምረት የሚያስቸለውን ማሽን ተከላ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

ፋንብሪካው በአሁኑ ወቅት ከ600 በላይ ለሚሆኑ ለአካበቢው ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ ማደረግ ጀምሯል።

ሰራተኞችን በስልጠና ከማብቃት ጀምሮ የትራንስፖርትና የምግብ አበል ማበረታቻ ማመቻቸታቸውንም  ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው በክልሉ ጎንደር፣ ባህር ዳርና ደብር ማርቆስ ከተሞች የጨርቃጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ፋብሪካዎች መቋቋማቸውን ገልጸዋል።

የጎንደሩ ፋብሪካ በግብዓትነት የሚጠቀመውን ምርት በሃገር ውስጥ እየተጠቀመ መሆኑን ጠቁመው  "በቀጣይም ምርቱን ወደ ውጭ  በመላክ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝበት መንገድ ይመቻቻል" ብለዋል።

በፋብሪካው ጉብኝትም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ፣ የፌደራልና ሌሎች የክልል አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግሮችን በመፍታት ምርታማነታቸውን ለማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሚመከረው መድረክ ከጉብኝቱ በኋላ በጎንደር ከተማ እንደሚካሄድም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም