ምክንያታዊና በውይይት የሚያምን ማህበረሰብ ለመፍጠር በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የሰላም ኮንፈረንስ መስፋፋት አለበት

51
ኢዜአ ታህሳስ10/2012 ምክንያታዊና በውይይት የሚያምን ማህበረሰብ ለመፍጠር በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የሰላም ኮንፈረንስ ማካሄድ እንደሚገባ ተገለጸ። ባለፉት ሳምንታት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የንግድ ማኅበረሰብ፣ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አንቂዎች፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖትና የማኅበረሰብ አመራሮች መካከል ሲካሄዱ የቆየው የሰላም ኮንፈረንስ የማጠቃለያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ዛሬ ተካሂዷል። ይህም የሰላም ኮንፈረንስ  "ለሁላችንም የምትመች ኢትዮጵያን በጋራ እንገንባ" በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ የቆየ ነው። በሰላም ኮንፈረንሱ የማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ እና የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል። የሰላም ኮንፈረንሱ ልዩነቶችን አስታርቆና አቻችሎ የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች ለማቀራረብ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰላም ኮንፈረንሱ ማጠቃለያ ፕሮግራም ተሳታፊዎች ''ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው'' ሲሉ ተናግረዋል። በዚህም የአገሪቱን ሰላም በዘላቂነት ለመጠበቅ የሰላም ኮንፈረንስ መዘጋጀት እንዳለበት አስገንዝዋል። መድረክ መመቻቸቱ ከስሜታዊነት ይልቅ ምክንያታዊ የሆነ ማህበረሰብን ለመፍጠር የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ ''እንደነዚህ ያሉ የሰላም ኮንፈረንሶች ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ መደረግ አለባቸው'' ብለዋል። የሰላም መኖርና መደፍረስ ጉዳይ የመንግስት ወይም የተወሰኑ ክፍሎች ጉዳይ ባለመሆኑ ሁሉም ህዝብ በሃላፊነት በአገሪቱ ሰላም፣ ልማትና እድገት ላይ የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባልም ብለዋል ። በመሆኑም ህዝቦች በሚያከፋፍሉና በሚያለያዩ ሃሳቦችና ተግባራት ሳይሆን አንድ በሚየደርጉ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት አለበትም ሲሉም ተናግረዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም