ምሁራን የምድር መረጃን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በማጥናት ለፖሊሲ አውጪዎች ሊያውሉ ይገባል

63
ኢዜአ ታህሳስ 10 / 2012  --ምሁራን የምድር መረጃን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በማጥናትና በማጠናቀር የፖሊስ እና የስትራቴጂ አውጪዎች እንዲጠቀሙበት መስራት ይኖርባቸዋል ተባለ። በአገሪቱ ውስጥ በመሬት አያያዝና አጠቃቀም ላይ የተሰሩ ጥናቶችን ጥቅም ላይ ለማዋልና ልምድ ለመለዋጥ  ያለመ መድረክ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ተካሂዷል። በመድረኩ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጡ ጥናት አቅራቢና ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የምድር መረጃና ምልከታ ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ቢያድግልኝ ደምሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ  በአገርቱ በመሬት አያያዝና አጠቃቀም ላይ በተሰሩ በርካታ ጥናቶች የልምድ ልውውጥ ማድረግና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ነው። በኮንፈረንሱ ላይ በውሃ፣ በእርሻ፣ በማህበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲሁም  የከተሞች እድገትን አስመልክቶ የተካሄዱ ጥናቶች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። "ምሁራን የምድር መረጃን  በአዳዲስ ቴክኖሎጂ  አጥንተው በማጠናቀር  ለፖሊሲና ስትራቴጂ አውጪዎች እንዲውሉ መስራት ይኖርባቸዋል" ያሉት ደግሞ  ከጥናት አቅራቢዎች መካከል የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጥናት  ምርምር ተቋም ባለሙያ ዶክተር ልኡልሰገድ ታመነ ናቸው ። እንደእሳቸው ገለጻ ዘርፉን በአዳዲስ ቴክኖሎጂ  በማጥናትና መረጃን በማጠናቀር ለፖሊሲና ስትራቴጂ አውጪዎች ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ጠቄማታው የጎላ ነው። "ቴክኖሎጂው የግብርና፣ የተፋሰስ ልማት ስራዎች እና የማዳበሪያን ጥቅም ማሳደግ"  ያስችላል ብለዋል። እንደ ዶክተር ልዑልሰገድ ገለጻ የምድር መረጃን በቴክኖሎጂ  በማጥናትና በማጠናቀር የግብርና ስራን ማዘመን ለአገር ዘርፈ ብዙ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ አለው። "በኮንፈረንሱ ላይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ባለሙያዎች የልምድ ልወውጥ ማድረጋቸው ለአገር ልማት የሚኖረው አስተዋጽኦው የጎላ ነው" ያሉት ደግሞ ከአማራ ክልል እንጂባራ ዩኒቨርሲቲ የመጡት  አቶ ፍቃዱ ተመስገን ናቸው። ከኦሮሚያ ክልል ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተጋብዘው በመድረኩ ጥናታቸውን ያቀረቡት አቶ ግርማ አለሙ በበኩላቸው፣ "በመሬት ላይ ጥልቅ ጥናት እና ምርምር በማድረግ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲገኝበት ማድረግ ይቻላል" ብለዋል። አርሶ አደሮች ከባህላዊ የዘር አጠቃቀም ወጥተው በትንሽ መሬት ላይ የተሻለ ምርት እንዲያገኙ በጥናት የተደገፈ ስራ መስራት ከምሁራኑ እንደሚጠበቅ ነው ምክረ ሃሳባቸውን ያቀረቡት ። ኮንፈረንሱ ለሁለት ቀናት የተካሄደ ሲሆን የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ጨምሮ ከጅማ፣ ከባህር ዳር፣ ከእንጂባራ እና ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ ምሁራን ተሳትፈዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም