ሰልፉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያመጧቸው የአመለካካት ለውጥ ውጤት ነው-ታዳሚዎች

50
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010 በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ያለው ሰልፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ ወዲህ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያመጧቸው የአመለካከት ለውጥ ውጤት መሆኑን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ የሰልፉ ታዳሚዎች ገለጹ። ሰልፈኞቹ ባለፉት ሶስት ወራት በሰላምና በአንድንነት ላይ የተጀመሩ ለውጦች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባና ከእነሱም የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። ከሶማሌ ክልል በሰልፉ ለመታደም የመጣው ኢብራሂም አብዱልቃድር ረጅም ርቀት ተጉዞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አመራር እየመጣ ላለው የኢትዮጵያዊነት የአንድነት መንፈስ ድጋፍ ለመስጠትና ለውጡ ዘላቂ እንዲሆን የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ለማረጋገጥ እንደሆነ ገልጿል። ሰልፉ የሁሉም ብሄር ብሄረሰብን ያካተተ መሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለፍቅርና ለልማት መቆሙንም የሚያመላክት እንደሆነ መታዘቡንም ተናግሯል። ከአዲስ አበባ ከተማ ሰልፉን ለመታደም ማልዶ መስቀል አደባባይ የተገኘው ብርሃኑ ጎንፋ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተፈጠረው የአንድነት መንፈስ እንዲቀጥል ያለውን ድጋፍ ለመግለጽ ሰልፉን እንደተቀላቀለ አመልክቷል። ከአፋር ክልል መጥቶ ሰልፉ ላይ የተገኘው አብዲ ቢያድ “የቦታ እርቀት ሳይገድበን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለሰልፉ እንደመጣን ሁሉ በልማትና በአንድነት ስራዎች ላይ የሚያጋጥሙን ተግዳሮቶች ሳይገድቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስቀመጡትን አቅጣጫዎች ሁላችንም ለመተግበር ልንተባበር ያስፈልጋል'' ሲል ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም