ለባለይዞታ የልማት ተነሺዎች ምትክ ቦታ በእጣ ተላለፈ

70

ታህሳስ 9/2012 የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ለ70 ነባር ባለይዞታ የልማት ተነሺዎች ምትክ ቦታ በዕጣ አስተላለፈ ፡፡

የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርቱ የልማት ተነሺዎቹና ሌሎች አካላት በተገኙበት ተከናውኗል ፡፡

የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መልካሙ ወርቁ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ከከተማው መስፋፋት ጋር ተያይዞ በተለይ በከተማው ዳርቻ አካባቢዎች በሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና መሰል ተግባራት በርካታ ባለይዞታዎች ከቦታቸው ይነሳሉ ፡፡

በመጀመሪያ ዙር ጥናት ተደርጎ የልማት ተነሽነታቸው ከተረጋገጡና ለመነሳት ዝግጁ ከሆኑ 1ሺህ 136 ተነሺዎች መካከል 394ቱ ነባር ባለይዞታ አርሶ አደሮች ናቸው ፡፡

እንዲሁም ጥናታቸው ተጠናቆ የፀደቀ 230 ባለይዞታዎች የሚገኙ ሲሆን በሂደት ላይ ያሉ ደግሞ 399 ባለይዞታዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

አቶ መልካሙ እንደገለፁት ዛሬ በዕጣ ምትክ ቦታ የተላለፈላቸው 70 ነባር ባለይዞታ አርሶ አደሮች ከታቦር ክፍለ ከተማ ፋራ ቀበሌ የሚነሱ ናቸው ፡፡

ምትክ ቦታ ማስተላለፍ መጀመሩ ተነሺዎች በወቅቱ በሚደርሳቸው ቦታ ላይ የተረጋጋ ኑሮ እንዲጀምሩ ፤ ለማይነሱት ደግሞ ለኑሮ ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን ለመፍጠር የሚረዳ እንደሆነም ተናግረዋል ፡፡

ቦታ የማስተላለፉ ሂደት ፍትሐዊነትን የተከተለ እንዲሆን ጥረት የተደረገ ሲሆን የሚነሱበትን የቦታ ስታንዳርድ ታሳቢ ያደረገ የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ስርዐት እንደተከናወነ አብራርተዋል ፡፡

ለነባር ባለይዞታዎች ቅድሚያ የተሰጠው ህጋዊ አሰራርን በመከተል እንደሆነ ያስረዱት ኃላፊው በቀጣይም ተከታታይነት ባለው መልኩ ለሌሎች ተነሺዎች ምትክ ቦታ የማስተላለፍ ስራ እንደሚከናወን ገልፀዋል ፡፡

ለዚህም አገልግሎት የሚሆን ተተኪ ቦታ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል ፡፡

ምትክ ቦታ በዕጣ ከተላለፈላቸው ነባር ባለይዞታ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሙሴ አታሮ በሰጡት አስተያየት ለሚነሱበት ቦታ ተመጣጣኝ ደረጃ ያለው ምትክ በዕጣ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

አቶ ያዕቆብ ቦርሳሞ በበኩላቸው አሁን ያለው የከተማው አመራር ችግራቸውን ለመቅረፍ የገባውን ቃል በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ማድረጉንና በዕጣ የማስተላለፍ ሂደቱም ፍትሐዊ እንደነበር አስረድተዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም