የዞኑ አርሶ አደሮች በታዳሽ ኃይል የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ በመጠቀም መስኖ እያለሙ ነው

159

ኢዜአ ታህሳስ 08 ቀን 2012 በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የታህታይ ማይጨው ወረዳ ሞዴል አርሶአደሮች ለመስኖ ልማት ሥራቸው ከጸሐይ ብርሀን በሚመነጭ ታዳሽ ኃይል የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ተግባራዊ አደረጉ። በወረዳው የማይስየ ቀበሌ አርሶ አደር አብርሃለይ አጽብሃ እንዳሉት በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ተጠቅመው የመስኖ ልማት ሥራቸውን እያከናወኑ ነው።

የውሃ ፓምፑ አጠቃቀሙ ቀላል ከመሆኑ ባለፈ የውሃ ማከፋፈያ መሳሪያ የተገጠመለት በመሆኑ ይባክን የነበረውን ጉልበት ውሃ እንደቀነሰላቸው ተናግረዋል።

ከእዚህ በፊት ለመስኖ አገልግሎት ከሚጠቀሙበት የውሃ ጉድጓድ ውሃ ለመሳብ የሚጠቀሙት በነዳጅ የሚሰራ ጀነሬተር እንደነበረ አስታውሰዋል።

ጀነሬተሩ ጉልበት የሚጠይቅ ከመሆኑ በተጨማሪ ከፍተኛ ወጪና የአካባቢ ብክለት ሲያስከትል አንደነበር አርሶ አደሩ ተናግረዋል።

"አዲሱ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ይህንን ችግራችንን ማስወገዱን በተግባር እያየን ነው" ያሉት አርሶ አደሩ፣ በአሁኑ ወቅት የውሃ ፓምፑን በመጠቀም ግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ቀይ ሽንኩርት እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ሴት አርሶ አደር አስካለ ገብረዋህድ በበኩላቸው ከጸሐይ ብርሀን በሚመነጭ  ታዳሽ ኃይል የሚሰራውን የውሃ መሳቢያ ፓምፕ በተያዘው ታህሳስ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ መጠቀማቸውን ገልጸዋል።

"የውሃ መሳቢያው ጉልበት እና የውሃ ብክነትን በመቀነስ ሥራችንን  ቀላል  አድርጎታል" ብለዋል።

እንደአርሶ አደሯ ገለጻ ቀደም ሲል የጉድጓድ ውሃ በመጠቀም አንድ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ከአምስት ሰው ጉልበት በላይ ይጠይቅ ነበር።

የውሃ መሳቢያ ፓምፑ የራሱ የውሃ ማከፋፈያ ስላለው በጥቂት የሰው ኃይል ሰፊ ቦታ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂውን ከመስኖ ልማት ባሻገር ለኤሌክትሪክ  መብራት እየተጠቀሙበት መሆናቸውንም አርሶ አደሯ አመልክተዋል።

"የውሃ መሳቢያ ፓምፑ ውሃ በመቆጠብ ሰፊ መሬት በመስኖ ለማልማት የሚያግዝ ነው" ያለው ደግሞ ወጣት አርሶ አደር ሀዱሽ ገብረ ነው።

እንደወጣቱ ገለጻ በአሁኑ ወቅት  አንድ ሄክታር መሬት በተለያዩ የጓሮ እትክልትና ሌሎች በገበያ ተፈላጊ ዮሆኑ ሰብሎች በቀላሉ እያለማ ነው።

በታሕታይ ማይጨው ወረዳ የመስኖ ባለሙያ የሆኑት አቶ ካሕሳይ ገብረዋህድ  በበኩላቸው  ለመስኖ ስራ የሚያግዝ ታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ በድጋፍ የተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

ኤጀንሲው የጸሐይ ታዳሽ ኃይልን ለመስኖ ልማት ለማዋል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሙከራ ሥራ እያከናወነ መሆኑንና ወረዳው የእዚህ ተጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ በሰርቶ ማሳያ ቴክኖሎጂ ሙከራ 20 የወረዳው አርሶ አደሮች በነጻ ተጠቃሚ ሆነዋል።

አርሶ አደሮቹ ከጸሐይ ብርሀን  የሚሰራ ኃይል በመጠቀም መስኖ ከማልማት በተጨማሪ  ለመብራት አገልግሎት እየተጠቀሙበት መሆኑንም አቶ ካሕሳይ ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂው  የካርቦን ልቀትን በመቀነስ በአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።

በወረዳው በበጋው ወቅት 1 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደስራ ተገብቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም