ለዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ በሥነ-ምግባር የታነጸ ዜጋ መፍጠር ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል

108

ኢዜአ ታህሳስ 8 ቀን 2012 በአገሪቱ ሰላምና ዴሞክራሲን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሥነ-ምግባር የታነጸ ዜጋ መፍጠር ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

ለዚህም ከቤተሰብ ጀምሮ የሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት በተቀናጀ መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ነው የተገለጸው።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከወላይታ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር በሰላምና አብሮነት፣ በሃይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነት እንዲሁም በመልካም ስነ-ምግባርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ያለሰላምና አብሮነት የሚገነባ ልማትና ሥልጣኔ ብዙም ውጤታማ አይሆንም፡፡

"ባለፉት ጊዜያት ለትምህርት ተደራሽነት የተሰጠውን ያህል ትኩረት ለውጤታማነትና ለግብረ-ገብነት አለመሰጠቱ ያለውን እያፈረሰ ሌላ የሚጠይቅ ትውልድ እንዲፈራ ምክንያት ሆኗል" ብለዋል፡፡

ይህን ለመቀየርና ሰላምና ዴሞክራሲን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ማፍራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

መንግስት በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራመሆኑን ያመለከቱት ፕሮፌሰሩ፣ "አገራዊ ማንነትና ዕሴት ላይ ትኩረት ያደረገው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ-ካርታ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል።

በተለይም የሃይማኖት ተቋማትና ቤተሰብ ለሰላም ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገ ነው ያሳሰቡት፡፡

"በስነ-ምግባር የታነጸና ግብረገብ የሆነ ዜጋ የመፍጠሩ ሥራ ነገን በማሰብ የሚከናወን ነው" ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ሃጂ መሱድ አደም ናቸው።

"ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች የተስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ለግብረ-ገብነትና ሥነ-ምግባር ባልሰጠነው ትኩረት ልክ የተከሰቱ በመሆናቸው ሁላችንም ከተጠያቂነት አናመልጥም" ብለዋል።

ችግሩን በዘላቂነት እንዲፈታ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር የጋራ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን የገለጹት ሃጂ መሱድ፣ በእዚህም ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በአስተምሯቸው ተከታዮቻቸውን ስለሰላምና አብሮነት እንዲያስተምሩ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የወላይታ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ አቶ ሚልክያስ ኦሎሎ በበኩላቸው በሃይማኖት ጽንፈኝነት የሚነሱ ችግሮች ለማንም የማይተርፉና ከሃይማኖታዊ አስተምህሮቶች ውጪ የሆኑ መሆናቸውን ገልጸው፣ ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሠላም ሚኒስቴር የሃይማኖትና ዕምነት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኃለፎም አባይ በበኩላቸው፣ ችግሮችን በጋራ በውይይት ለመፍታትና አብሮነትን ለማጎልበት የአገራዊ ዕሴቶች ያላቸውን ፋይዳ ለወጣቱ ትውልድ ማስተዋወቅ፣ ማስተማርና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

"የእኔ ብቻ የሚሉ አስተያየቶች አደገኛና ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ የተጀመረው  ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን የመገንባት ሂደት ውጤታማ እንዲሆን መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች የተውጣጡ የሃይማኖት መሪዎችና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም