አካል ጉዳተኞችን የዘላቂ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ተባለ

65
ታህሳስ 7/2012 አካል ጉዳተኞችን የዘላቂ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግና በእኩልነት ለማሳተፍ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአካል ጉዳተኞች ገለጹ። በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች በፓናል ውይይቶችና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በኢትዮጵያ ለ27ኛ ጊዜ ሲከበር የሰነበተው የአካል ጉዳተኞች ቀን የማጠቃለያ ዝግጅት ዛሬ ተደርጓል። በበዓሉ ላይ የታደሙት አካል ጉዳተኞች በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት ጊዜያት በአገሪቷ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎች አካል ጉዳተኞች ከግምት ውስጥ አይገቡም ነበር። ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ ማሞ ተሰማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት የአካል ጉዳተኛውን ማህበረሰብ የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረው እንቅስቃሴ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል። ሌላኛዋ ተሳታፊ መምህርት ሲሳይ ጸሃይ አካል ጉዳተኝነት ማለት አለመቻል ባለመሆኑ እንደ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍል እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማብቃት ስራ የሁሉም አካል ሃላፊነት እንደሆነ ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ የአካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ንጉሴ ግደይ በመድረኩ ባሰሙት ንግግር፤ ''የአካል ጉዳተኞችን ችግሮች ለማቃለልና በልማት ስራዎች ተሳታፊ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ጅምር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው'' ብለዋል። ይህን እውን ለማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚወስዳቸው እርምጃዎች ዘላቂነት ሊኖራቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የከተማ አስተዳደሩ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አለምጸሃይ እንደገለጹት፤ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የአካል ጉዳተኛውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ጥናት ተደርጓል። በጥናቱ ከ13 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 43 በመቶ ሴቶች ናቸው። ከእነዚህም መካከል 69 በመቶ የቤተሰብ ሃላፊ፣ 53 በመቶ ከ1እስከ 3 ሰዎች የሚያስተዳድሩ፣ 45 ነጥብ 5 ምንም ያልተማሩ፣ 6 ነጥብ 5 ዲፕሎማና ዲግሪ ያላቸው እንደሆኑ የቢሮ ሃላፊዋ ገልጸዋል። በጥናቱ ላይ ከተሳተፉት አካል ጉዳተኞች መካከልም 23 በመቶ መደበኛ ገቢ ያላቸው፣ ከ11 በመቶ በላይ ጡረተኞች፣ 30 በመቶ ተጠግተው የሚኖሩ የሚኖሩ ናቸው። 77 በመቶ የሚሆኑ አካል ጉዳተኞች በኪራይ ቤት የሚኖሩ እንደሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል። በመሆኑም መንግስት ከምን ጊዜውም በላይ አካል ጉዳተኞችን በልማት ስራዎች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታሳቢ ያደረገ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል። በዚህም በምገባ ምክንያት በ2011 ዓ.ም. ትምህርትያቋረጡ ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባና የዩኒፎርም ተጠቃሚ በማድረግ  ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስታውሰዋል። አካል ጉዳተኞች የራሳቸው የሆነ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸውም በሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ፣ ልዩ የብድር አቅርቦት ለወጣቶችና ያለ እድሜ ገደብ ብድር መመቻቸቱንም ገልጸዋል። በቀጣይም አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከከተማ አስተዳደሩና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር  በትኩረት እንደሚሰራ ተገልጿል። በቅርቡ የወጡ ዓለም አቀፍ መረጃዎችና ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛቷ 18 በመቶ የሚሆኑት የአካል ጉዳተኞች ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት ከድህነት ወለል በታች  ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም