ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ድጋፍ ለመስጠት በድሬዳዋ ሰልፍ ሊካሄድ ነው

78
ድሬዳዋ/ደሴ/ ጎንደር ሰኔ 15/2010 ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የለውጥ እንቅስቃሴ ድጋፍ ለመስጠት በመጪው እሁድ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በድሬዳዋ እንደሚካሄድ የሰልፉ አስተባባሪ ወጣቶች ገለጹ። ይኸው የድጋፍ ሰልፍ በጎንደርና ደሴ ከተሞችም እንደሚካሄድ ተመልክቷል። በድሬዳዋ የሰልፉ አስተባባሪዎች ዛሬ ማምሻውን ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት ሰልፉን ለማካሄድ የሚያስፈልገው ዝግጅት ተጠናቋል። አስተባባሪዎቹ እንዳሉት "እኛ ድሬዎች ጥሪህን ሰምተን ተደምረናል" በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ቁጥራቸው እስከ 100 ሺህ የሚደርስ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ ወጣት እንድሪያስ ተካልኝ እንደተናገረው ሰልፉ ህጋዊ ዕውቅና እንዲላበስ ለድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያቀረቡት ጥያቄ ዕውቅና አግኝቶ የሰልፉ ቅስቀሳ በገጠርና በከተማ እየተካሄደ ይገኛል። "እኛ ድሬዎች ጥሪህን ሰምተን ተደምረናል" የሚል መልዕክትና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ምስል ያለበት ቲሸርት ለሰልፉ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡ በሰልፉ ቁጥራቸው እስከ መቶ ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፣ ህዝባዊ ሰልፉ ያለምንም የጸጥታ ችግር ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ እንደ ወጣት እንድሪያስ ገለጻ የሰልፉ ዋና ዓላማ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ለአገር አንድነት፣ ሠላምና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መረጋገጥ ሁነኛ መንገድ መሆኑን ማሳወቅና ጅምር ተግባራቱን ከዳር ለማድረስ ህዝቡ ከጎኑ ለመቆም ዝግጁ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ህዝባዊ ሰልፉም የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የብልጽግና አገር እንድትሆን በመደመር መስራት ይገባናል ያሉትን ጥሪ በመቀበልና ህዝቡ ከጎናቸው እንደሆነ ለመግለጽ የተዘጋጀ ጭምር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የኮሚቴ አባል ወጣት አኒሳ አብዲ በበኩሏ የነገው የአዲስ አበባ ሰልፍ እንዳይደበዝዝ ሲባል ሰልፉ እሁድ እንዲካሄድ መደረጉን ተናግራለች። ከከተማ ዋና ዋና ሥፍራዎችና በከተማው አቅራቢያ ከሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች የሚመጡ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ለገሀር አደባባይ በመገኘትና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ብቻ በማንገብ የሰላም፣ የአንድነትና የፍቅር መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ። የሰልፉ ማሳረጊያም በስታዲዮም ውስጥ እንደሚሆን አመልክታለች፡፡ ከነገ በስቲያ እሁድ የሚካሄደው ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በሰላም እንዲጠናቀቅ ፍቅርና ሕብረትን የተላበሰው የድሬዳዋ ህዝብ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የተለመደ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ኮሚቴው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ በተያያዘ ዜና በአማራ ክልል በጎንደርና ደሴ ከተሞችና አካባቢው ያሉ ነዋሪዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ በነገው ዕለት በየከተሞቹ ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚካሄዱ ታውቋል፡፡ ከንጋቱ 12፡30 ጀምሮ በሚካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም