ሚዲያው ለአየር ንብረት ለውጥ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

71
ታህሳስ 6/2012 ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ እየወሰደች ያለው ተነሳሽነት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚዲያ ዘርፉ ሚናውን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ተባለ ። ሚዲያው ለዘርፉ ለውጥ የድርሻቸውን እንዲወጣ የሚያስችለው ስልጠና እየተሰጠ ነው። ስልጠናው የምስራቅ አፍሪካ አገራት ቀጠናዊ አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ከወዲሁ እንዲከላከሉ ለማስቻል በሚሰራው ”ዱኒያ” በተሰኘው ፕሮጀክት የተዘጋጀ ነው። በዚህም የአገራችንን ጨምሮ ከኬንያና ከኡጋንዳ ለተውጣጡ  የሚዲያ አካላት፣ ጋዜጠኞችና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የተሰማሩ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች እየተሳተፉ ነው። በስልጠናው ላይ ኢትዮጵያ  ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የተፈጥሮ ሁነቶችን ለመከላከል በተቋምና በማህበረሰብ ደረጃ የተለያዩ ወቅታዊ አጀንዳዎችን ቀርጻ እየተንቀሳቀሰች መሆኗ ተገልጿል። ስልጠናው በመንግስት በኩል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝና የሚዲያ ዘርፉም የአየር ንብረት ለውጥ ነክ አጀንዳዎችን በአንገብጋቢነት ይዘው እንዲያካትቱ ያስችላልም ተብሏል። ስለሆነም ሚዲያውን ጨምሮ ጋዜጠኛው ህብረተሰቡን የማንቃት ኃላፊነቱን ሙያዊ በሆነ መልኩ እንዲወጣ ነው የተነገረው። በተለይም ጋዜጠኞች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ቀጠናዊና ከባቢያዊ ዘገባዎቻቸውን ክስተቱ ያደረሰውን ችግር ከመንዛት ወጥተው ቅድመ-መፍትሔዎችን ማስገንዘብ ላይ እንዲያተኩሩ ያዘጋጃቸዋል ተብሏል። ከኒው ቢዝነስ ኢትዮጵያ የድረ-ገጽ ጋዜጠኛ አንዱዓለም ሲሳይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የአየር ንብረት ለውጥ  ተጽዕኖው የሁሉም በመሆኑ ከሚዲያውና ከጋዜጠኛው ብዙ ይጠበቃል ብለዋል። አብዛኞቹ የአገራችን ሚዲያዎች በተለይም ጋዜጠኞች አጀንዳቸውንና ዘገባቸውን በአየር ንብረት ላይ ለምን እንደማያደርጉ ኢዜአ ላነሳው ጥያቄ ፍላጎት ያለመኖር ሳይሆን ሙያዊ ክፍተት እንዳለ ተጠቁመዋል። በሚዲያውና ጋዜጠኞች ስለአየር ንብረት አዘጋገብ የነበሩ ሙያዊ ክፍተቶችን ስልጠናው ሊሞላ እንደሚችል ገልጸው ባገኙት ክህሎት ጋዜጠኞችም በሙያቸው የመንግስትን ተነሳሽነት እንደሚያግዙ ነው፤ ጋዜጠኛ አንዱዓለም ያስረዱት። የፕሮጀክቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሚነሪ ፍሎረንስ በበኩላቸው ሚዲያው በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያለውን አበርክቶ ከማሳደጉም በላይ ስጋቱን ለመቀነስ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም የኢትዮጵያ፣ የኬንያና የኡጋንዳ ጋዜጠኞች እንደሚሳተፉ ነው የተናገሩት። ወደ ፊትም ተመሳሳይ ስልጠናዎች በፕሮጀክቱ ለተመረጡ አገራት ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች በቀጥታና በኦን ላይን እንደሚሰጥ ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም