ኢህአፓ ለመመዝገብ የምርጫ ቦርድ የሚጠይቀውን የአባላት ቁጥር ማሰባሰቡን አስታወቀ

58
ታህሰሳስ 6/2012 የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ለመመዝገብ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲ የሚጠየቀውን የደጋፊ አባላት ማሰባሰቡን አስታወቀ። ፓርቲው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ መሰረት በማድረግ ከተለያዩ ክልሎችና ከከተማ መስተዳደሮች  ከ10ሺህ በላይ የደጋፊዎች ፊርማ ማሰባሰቡን ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስተውቋል። ፓርቲው ታህሳስ 4 እና 5 ቀን 2012 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ባካሄደው ጉባኤ  ከ500 በላይ ከተለያዩ  የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ አባላት እና በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በመሳተፍ አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን  የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ተሰማ  አስታውቀዋል። በወቅቱ  የፓርቲውን አላማ፣ርዕዮት አለም፣ ህግና ደንብ፣ ፕሮግራም፣ ስያሜና አርማ ላይ  ክርክር ተደርጎ  ስምምነት ላይ ተደርሶ መጽደቁ ተገልጿል። ''ኢህአፓ የተሻለ ስራ ለመስራት ነባር አመራሮችን በአዳዲስ አመራር የመተካት ስራ ተሰርቷል፤ በዚህም ጓዲት ቆንጅት ብርሃን የፓርቲው መሪ፣ ጓድ ጳውሎስ ሶርሳ የፓርቲ ሊቀመንበር በመሆን ተመርጠዋል'' ብልዋል። የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ተሰማ  በምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ መሰረት የደጋፊዎችን ፊርማ  ለማሰባሰብ በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ እንደነበር አስታውሰዋል። በተደረገው እንቅስቃሴም ከ10ሺህ በላይ  የደጋፊዎች ፊርማ ተሰብስቦ በምርጫ ቦርድ ለመመዝገብ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል። ''ፓርቲው በአዲሰ መልክ አመራሮችን የመረጠው የቀድሞው አመራሮች በውጭ አገር የሚኖሩና ለስራ አመች ካለመሆኑ በላይ ወቅቱ ወጣት አመራር የሚጠይቅ ስለሆነ ነው'' በማለት አብራርተዋል። በቀጣይ የፓርቲውን አመራርና አባላቱን በማጠናከር  የሃሳብ ተመሳሳይነት ካላቸው ፓርቲዎች ጋር በትብብር በመስራት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን እንደሚሰራ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ  ባለፉት 44 ዓመታት በአገሪቱ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ሲታገል እንደነበርም አስታውቋል። በአገሪቱ የተደረገውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ  ወደ አገር ቤት በመግባት ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝም ተገልጿል። ኢህአፓ ለዴሞክራሲና ለአገር አንድነት ትግል በሚያካሂድበት ወቅት ለጠፋው የሰው ህይወትና ንብረት ከትናንት በስቲያ ለመጀመሪያ ጊዜ አመታዊ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ማካሄድ ሲጀምር በይፋ ይቅርታ መጠየቁ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም