የአርበኞች ግንቦት 7 ምንም አይነት የአመፅ እንቅስቃሴ ከማድረግ መታቀቡን አስታወቀ

108
አዲስ አበባ ሰኔ15/2010 የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ንቅናቄ ከዛሬ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም አይነት የአመፅ እንቅስቃሴ ከማድረግ መታቀቡን አስታወቀ። ንቅናቄው ከድርጊቱ የታቀበው በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ በአገሪቷ ህዝብ ውስጥ እየታየ ያለውን የሰላም፣ የፍትህና ተያያዥ ለውጦችን መሰረት በማድረግ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በአገሪቷ እየመጣ ያለው ለውጥ ከግብ እንዲደርስ "ከኢትዮጵያ ህዝብና ለውጡን ከሚመራው ወገን ጎን እቆማለሁ"ሲል አብራርቷል። ይህንንም ተከትሎ በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ የሚገኙ የንቅናቄው አባላት ከማንኛውም አመፅ ቀስቃሽና ህገ ወጥ ተግባር እንዲታቀቡ ትዕዛዝ ማስተላለፉን አስታውቋል። "በአሁኑ ወቅት ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲ ሊወስደን የሚችለው ከማንኛውም አመፅ ነፃ የሆነ ሰላማዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ትግል ነው " በማለት በመግለጫው የገለጸው ንቅናቄው፤ አሁን የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ገጽታውን ይዞ እንዲሄድ ለማበረታታት የታለመ በራስ ተነሳሽነት የተወሰደ ውሳኔ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም