የብልጽግና ፓርቲ አግላይነትን በማስቀረት ሁሉንም አሳታፊ የሚያደርግ ነው--- በቤንች ሸኮ የፓርቲው ሰብሳቢ

47

ታህሳስ 5/2012 ኢዜአ የብልጽግና ፓርቲ ባይተዋርነትና አግላይነትን በማስቀረት ሁሉንም አሳታፊ የሚያደርግ መሆኑን በቤንች ሸኮ ዞን የብልጽግና ፓርቲ  የፓርቲው ሰብሳቢ ገለጹ። በፓርቲው አስፈላጊነት፣ ቀጣይ አቅጣጫና ህገ ደንብ ዙሪያ ከቤንች ሸኮ ዞን ወረዳና ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ አመራሮች ጋር በሚዛን አማን ከተማ ውይይት ተጀምሯል።

በውይይቱ ወቅት በዞኑ የብልጽግና ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ፍቅሬ አማን እንዳሉት ውህደቱ ከዚህ በፊት የነበረውን አግላይነትን በማስቀረት ሁሉንም አሳታፊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

"የኢህአደግ የአጋር ድርጅቶች  ውህደት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሲቀርብ የቆየ ጉዳይ ነው" ያሉት አቶ ፍቅሬ ሀገራዊ ስጋቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል።

ውህደቱ ተፈፃሚ መደረጉም ባይተዋርነትንና አግላይነትን በማስቀረት ሁሉንም የሚያሳትፍ ፓርቲ ለመመስረት ያግዛል።

"ይህም አዲሱ የብልፅግና ፓርቲ ጠንካራና አቅም ያለው ሀገር አቀፍ  እንዲሆን ያስችለዋልም "ብለዋል።

በዞኑ  ፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት ምናሴ በበኩላቸው " በብልጽግና ፓርቲ አስፈላጊነትና ሀገራዊ ፋይዳ ዙሪያ የሚደረገው ውይይት እስከ ቀበሌ ይቀጥላል "ብለዋል።

ፓርቲው  ህብረብሔራዊነትን የሚያስተናግድና ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በደቡብ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ተወካይ አቶ አማኑኤል አብደላ በበኩላቸው ውህደቱ ብሐራዊ  መግባባት በመፍጠር ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ እኩል የሚሳተፉበት ዕድል እንሚፈጥርም አስረድተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረክ ከቤንች ሸኮ ዞን ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም