መንግስት የነገው የድጋፍ ሰልፍ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ

107
አዲስ አበባ ሰኔ15/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ላመጧቸው ለውጦች ድጋፍና እውቅና መስጠትን ዓላማ አድርጎ በአዲስ አበባ የሚደረገው ሰልፍ በስኬት እንዲጠናቀቅ መንግስት አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ። የድጋፍ ሰልፉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ማደረጉን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፤ የድጋፍ ሰልፉ በስኬት እንዲጠናቀቅ መንግስት አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቋል። የነገው የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር ቀን መሆኑን የገለጹት አቶ አህመድ የድጋፍ ሰልፉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ የራሱ ሰላም ጠባቂ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ መንግስት የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ማበረታቻ የሚሆን ብቻ ሳይሆን መንግስት የጀመረውን የለውጥ ሥራዎች በይበልጥ ለማጠናከር ቃል የሚገባበት እንደሚሆንም አመልክተዋል። በዚህ ሰልፍ ኢትዮጵያ ቀጣይ ሰላሟ እንዲረጋገጥ መላው ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ኃይማኖት፣ ብሄርና የፖለቲካ አመለካከት ሳይሉ በዚህ ሰልፍ ላይ በመሳተፍ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘይኑ ጀማል በበኩላቸው በሰጡት መግለጫ ፖሊስ የሰልፈኛውን ደህንነት ለመጠበቅ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ ብዛት ያለው ህዝብ ከከተማው ውስጥና ውጪ ተሳታፊ ይሆናል ተብሎ ስለሚጠበቅ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ኮሚሽነር ጄኔራሉ አሳስበዋል። በሰልፉ ላይ እንዲገኙ የተጋበዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም