የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ እንዲመዘገብ መወሰኑ ለቱሪስት ፍሰት ማደግ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው

61
ኢዜአ ታህሳስ 04 2012 ---የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንደሚዘገብ መወሰኑ ለቱሪስት ፍሰት ማደግ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን በአክሱም አስተያየታቸውን የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። በዓሉ በዓለም አቀፍ የቅርስ መዝገብ እንዲመዘገብ መወሰኑ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸው ውሳኔው በቀጣይም ሌሎች ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላትን ለማስመዝገብ እንደሚያነሳሳ ተናግረዋል። የርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ ቦክረ ሊቃውንት ጎደፋ መርሃ እንዳሉት በውሳኔው እሳቸውም ሆነ የአካባቢው ህብረተሰብ ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ነው የገለጹት። ምክትል ሰብሳቢው የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ መወሰኑ በተለይ ለቤተ ክርስቲያኗ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል። "ውሳኔው ህብረተሰቡ በዓሉን ይበልጥ በድምቀት እንዲያከብር፣ የበዓሉን ትውፊቱንና ስርአት ጠብቆ  እንዲቆይና በአገሪቱ የቱሪስት ፍሰት እየጨመረ እንዲመጣ ያደርጋል'' ብለዋል። በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ብቻ በየወሩ ለሰባት ቀናት የሚደረገውን የምህላ ሰነ ስርአት ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ እና ለማስመዝገብ እንደሚሰሩም ቦክረ ሊቃውንት ጎደፋ ተናግረዋል። የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድሀን ፍጹምብርሃን በበኩላቸው የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ መደረጉ ለክልሉ እና ለአገሪቷ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል። "ቱሪስቶች በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶችን መሰረት በማድረግ ነው ለጉብኝት የሚንቀሳቀሱት" ያሉት ኃላፊው ውሳኔው የውጭ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን የጉብኝት መዳረሻ እንዲያደርጉ በማድረግ በኩል ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አመልክተዋል። በዓለም ቅርስነት ለመዘገቡ የሚችሉ ሌሎች ብዙ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት እንዳሉም አቶ ገብረመድህን ተናግረዋል። የአክሱም ጽዮን እና  የአሸንደ (ዓይኒዋሪ) በዓላት በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት ከሚደረግባቸው ለአብነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ መወሰኑ በቀጣይም መንግስትና ህዝቡ ሌሎች በርካታ በዓላትን ለዓለም ማህበረሰብ በማስተዋወቅና በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጠንክረው እንዲሰሩ መልዕክት ያስተላለፈ ክስተት መሆኑንም  አቶ ገብረመድሀን  ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም