የምርት ብክነትን ለመቀነስ የተሻሻሉ የምርት ማከማቻ ከረጢቶችን ለአርሶ አደሩ ማስተዋወቅና ተደራሽ ማድረግ ይገባል

79
ኢዜአ ታህሳስ 04 / 2012…የሕብረት ሥራ ማህበራት በድህረ ምርት የሚኖረውን ብክነት ለመቀነስ የተሻሻሉ የምርት ማከማቻ ከረጢቶችን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅና ተደራሽ በማድረግ ላይ አተኩረው ሊሰሩ እንደሚገባ የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጄንሲ አስገነዘበ። በድህረ ምርት አያያዝ የተሻሻሉ የማከማቻ ቴክኖሎጂዎችን ለመሰረታዊ ማህበራትና ዩኒዬኖች ለማስተዋወቅ ያለመ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል። የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ሱሩር በእዚህ ወቅት እንዳሉት የህብረት ሥራ ማህበራት በድህረ ምርት የሚኖረውን ብክነት ለመቀነስ የተሻሻሉ የምርት ማከማቻ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ማስተዋወቅና ተደራሽ ማድረግ አለባቸው። "አርሶ አደሩ ምርቱን በጥራት ለመያዝና በአገር ውስጥና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን በፀረ ተባይ ኬሚካል የታከመ ከረጢት በስፋት እንዲጠቀም ለማድረግ ማህበራቱ በሙሉ አቅማቸው መስራት ይኖርባቸዋል" ብለዋል። እንደ አቶ ዑስማን ገለጻ በአገር አቀፍ ደረጃ ከምርት አያያዝ ጋር ተያይዞ በሚከሰት ችግር ከ15 እስከ 30 በመቶ ብክነት ይፈጠራል። "ከእዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ የጥራት ጉድለት በማስከተል ምርቱ በገበያ ላይ ተፈላጊ እንዳይሆን ያደርጋል "ብለዋል። እንደዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ከ13 ሚሊዮን በላይ ለተባይ የተጋለጠና በኬሚካል ያልታከመ ከረጢት ለምርት መያዣና ማካማቻ እየተጠቀመ ነው። ይሁንና የግብርና ምርቶችን ከተባይ መከላከልና ለረዥም ጊዜ ማቆየት የሚችሉ የተሻሻሉ የማከማቻ ከረጢቶችን የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ቁጥር አነስተኛ ነው። ለምርት ጥራት፣ ተወዳዳሪ ለመሆንና፣ በአገር ውስጥና በውጭ ገበያ ምርትን በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ  ቴክኖሎጂው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል። "የሕብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒዬኖች ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብረው በመስራት ቴክኖሎጂውን ማስተዋወቅና ሁሉም አርሶ አደሮች ዘንድ እንዲደርስ ማድረግ አለባቸው" ብለዋል። በኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ማህበራት ፌዴሬሽን የሰብል ልማትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ ዘበነ ለማ በበኩላቸው ባለፈው በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ቴክኖሎጅውን የማስተዋወቅና ተደራሽ የማድረግ ሥራ መሰራቱን  ገልጸዋል። በእዚህም በድህረ ምርት በተለይም በክምችት ወቅት ሊኖር የሚችለውን ብከነት መቀነስ እንደተቻለ ገልጸው፣ በተያዘው የበጀት ዓመት 5 ሚሊዮን የሚሆኑ አርሶ አደሮች በመሰረታዊ ማህበራትና ዩኒዬኖች በኩል የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በአጠቃቀም ወቅት ሊኖር የሚችለውን ክፍተት ለመሙላት ለአርሶ አደሩ የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱንም አቶ ዘበነ ተናግረዋል። "አርሶ አደሩ ዓመቱን ሙሉ የለፋበት ምርት በነቀዛና በሌሎች ተባዮች እንዳይጎዳ ከህብረት ሥራ ዩኒዬኖች ጋር በትብብር እየሰራን ነው" ያሉት ደግሞ የዕድሜ ዓለም እጅጉ ቢዝነስ ግሩፕ ሥራ አስኪይጅ አቶ እድሜዓለም እጅጉ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በኬሚካል የታከመ የምርት ማከማቻ ከረጢት ለአርሶ አደሩ እያቀረቡ መሆኑንም ገልጸዋል። በመድረኩ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ የመሰረታዊ ማህበራትና ዩኒዬኖች አመራሮች ተሳታፊ ሆኖዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም