የሕክምና ባለሙያዎችን የአበረታች ቅመሞች ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል

82

ኢዜአ ታህሳስ 4 ቀን 2012 ኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎቿን የአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎችን በስፋት መስራት እንደሚገባት ተጠቆመ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት ለፋርማሲ ባለሙያዎችና ባለቤቶች በአበረታች ቅመሞች ዙሪያ ስልጠና እየሰጠ ነው።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገሪቷ አትሌቶች ላይ በተደረገ የአበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ ምርመራ ዘጠኝ አትሌቶች ቅመሙን አላግባብ ተጠቅመው በመገኘታቸው ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

ጉዳያቸው በሂደት ላይ የሚገኝ ሌሎች ሁለት አትሌቶች መኖራቸውንም ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ይህን ችግር ለመፍታት እንደ አገር የተቋቋመው ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችና ጎን ለጎንም የምርመራ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ከስራዎቹ መካከል ለፋርማሲ ባለሙያዎችና ባለቤቶች እየተሰጠ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ይጠቀሳል።

ስልጠናው በዋናነት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ በሚባሉት መድሃኒቶችና በዚሁ ዙሪያ የተቀመጡ የሕግ ጉዳዮችን የተመለከተ ነው።

ስልጠናውን የሰጡት ዕጩ ዶክተር ሰለሞን አሰፋ እንደ አገር በአበረታች ቅመሞች ወይም መድሃኒቶች ዙሪያ ባለሙያዎች በትምህርት ተቋማት በነበሩ ጊዜ በቂ ግንዛቤ አልተፈጠረላቸው ይላሉ።

ይህ የሆነው አበረታች ቅመሞች እንደ አገር የቅርብ ጊዜ ችግሮች በመሆናቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ችግሩን ለመከላከል ለፋርማሲና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ስልጠናዎችን በሰፊው በመስጠት ግንዛቤቸውን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል የፋርማሲ ባለሙያዎችና ባለቤቶች የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን ለመከላከል በሚሰራው ስራ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

አበረታች መድሃኒቶችን ያለአግባብ በሚሸጡና ሕጉን በሚተላለፉ መድሃኒት ቤቶች ላይ ከሚወሰደው አስተዳደራዊ እርምጃ ባሻገር ግለሰቦችም እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት ይጠብቃቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም