የትግራይ ሰማዕታት ቀን በመቀሌ ከተማ በሰላማዊ ሰልፍ ተከበረ

95
መቀሌ ሰኔ 15/2010 የትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞንና የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች 30ኛውን ዓመት የትግራይ ሰማዕታት ቀን ዛሬ በደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ አከበሩ። ቀኑ በመቀሌ ሰማዕታት ኃውልት ሲከበር ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የሀገር መከላከያና የፖሊስ ሠራዊት አባላት፣ ምሁራን፣ ተማሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ነባር የህወሓት ታጋዮች ተገኝተዋል። ነዋሪዎቹ ቀኑን ምክንያት በማድረግ ባካሄዱት ሰልፍ ላይ እንዳሉት ዕለቱ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ቃላቸውን ዳግም የሚያድሱበት ነው። በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን የተጀመረው ጥረት ከዳር እንዲደርስ ‘‘የሰላም አምባሳደር‘‘ እንደሚሆኑም ባሰሙት ድምጽና በያዟቸው መፈክሮች አረጋግጠዋል። ከነዋሪዎቹ መካከል በመቀሌ ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ ብርሃን ደስታ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ለሰፈነው ሰላምና ልማት መረጋገጥ የተከፈለውን መስዋዕትነት የመጠበቅ ኃላፊነት የአሁኑ ትውልድ ነው። የተጀመረው ሰላምና ልማት ዘላቂ እንዲሆን የማረጋገጥ ሥራ እውን እንዲሆን ከህዝብና ከመንግስት ጎን ሆነው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። "ሰማዕታትን በመዘከር እስካሁን የተቀናጀናቸውን የልማት ስኬቶች ማጣጣም አለብን" ያሉት ደግሞ ሌላዋ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ስምረት ሀፍቱ ናቸው። በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው ከአጎራባች አገሮች ጋር በተለይ ከኤርትራ ጋር በሰላምና በልማት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ግኑኝነት ሲኖር ብቻ መሆኑም ተናግረዋል። በመላው አገሪቱ በተለይ በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት የተረጋገጠው ሰላምና ልማት የሰማዕታት ውጤት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ ከድር አብዱርህማን ናቸው። የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ቀኑ ሲከበር ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፣ ህዝቡ የሰማዕታት ቀንን ሲያከብር አደራቸውን ጠብቆ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ በመነሳት ነው። ሁሉም ዜጋ በተለይ ወጣቱ ተውልድ የአባቶቹን ታሪክ የመጠበቅና አዲስ ታሪክ የመስራት ኃላፊነት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም