“አሸብራቂው መሪ ”

92

እንግዳው ከፍያለው  ባህርዳር /ኢዜአ/ ዓለማችን የ7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ህዝብ መኖሪያ ናት ። ታዲያ! በዚህ ምድር ላይ ህዝቦች እራሳቸውንና አገራቸውን በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ ለማስጠራት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ ። የሚሳካላቸው ግን ጥቂቶቹ ናቸው ።

ሰው ሆኖ የተፈጠረ ሁሉ ምኞቱ ብቻ ሳይሆን ግቡም ታላቅ መሆን ነው። ከግቡ ለመድረስም ሌት ከቀን ይጥራል ይለፋል ፣ ይደክማል፣ይታትራል። ውጤቱ ደግሞ የረጅም ጊዜ ልፋት እንጂ የአጭር ጊዜ ክስተት ሊሆን አይችልም።

ለስኬትም ሆነ ለውድቀት አጀማመር ወሳኝ ነው። በእርግጥ በመልካም የተጀመረ ሁሉ ፍሬው ያማረ ነው ብሎ መደምደምም  የዋህነት ነው።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ዛሬ ላይ በምድራችን ከሚገኙ የሰው ልጆች በሙሉ ተመርጠው የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ለመሆን የበቁት ገና ስልጣን ከመያዛቸው አስቀድሞ ትክክለኛውን መንገድ በመጨበጣቸው ነው የሚል እምነት አለ።

ትክክለኛ መንገድ ወደ ራዕዩ የሚያደርስ አስፓልት የለበሰ ወይም ተስተካክሎ የተሰራ የጥርጊያ መንገድ መሆኑን ከዶክተር ዓብይ ጉዞ ማረጋገጥ ይቻላል። ወንዙንና ሸለቆውን የሚያሻግር ድልድይ የተገነባለት መንንገድ መሆኑንም መዘንጋት አይኖርብንም።

“ተሰጥኦ ለሁሉም አይሰጥም ይላሉ” ኮርያዎች። የፖለቲካ ፣ የሳይንስ ፣ የፈጠራ ተሰጥኦ… ለሁሉም ህዝብ ሳይሆን ለተመረጡ ግለሰቦች የሚሰጥ መሆኑን አስምረው ይናገራሉ። አገርን ለማሳደግና የህዝብን አንገት በዓለም አደባባይ ቀና ብሎ እንዲሄድ ከተፈለገ “የመንግስትና የህዝብ ሚና ተሰጥኦ ያላቸውን ግለሰቦች በማፈላለግ ተንከባክቦ ወደሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ ነው” የሚል መልካምና ገዥ አባባል አላቸው።

ለዚህም ነው ያችን 50 ሚሊዮን የሚኖርባት የበሬ ግንባር የምታክል አገር ከስምንት በላይ ግዙፍ ኩባንያዎችን ለዓለም ያበረከትችው። ማበርከት ብቻም ሳይሆን በአለም ከበለጸጉ አገራት መካከል 11ኛ ተርታ ተሰልፋ የምትገኘው - ኮርያ ።

ኮሊኒ የሚባል የዮንሃፕ ኒውስ ኤጀንሲ ጋዜጠኛና ኮሪያዊ ጓደኛዬ በአንድ ወቅት ስለጉዳዩ ጠይቄው እንዳብራራልኝ ከሆነ “የኮርያ ህዝብና መንግስት ሳምሰንግ ፣ ሃዮንዳይ የመኪናና የመርከብ ኩባንያ፣ ኤል ጂ ኤሌክትሮኒክስ፣ ፖስኮ ብረታ ብረት፣ ኪያ ሞተርስ፣ ኤስኬ ቴሌኮምና ኦይል ሪፋይነሪና ሌሎች ኩባንያዎች የተመሰረቱት ተሰጥኦ ባላቸው ግለሰቦች ነው አለ” ።

የብረታ ብረት ኩባንያው ፖስኮ ከፍተኛ ሃብት የሚጠይቅ በመሆኑ እሱ ብቻ ነው በመንግስት ተመስርቶ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ለግል ባለሃብት የተዛወረው። በ1970ዎቹ የተመሰረቱት እነዚህ ኩባንያዎችበዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የኮርያ መንግስትና ህዝብ መስዋዕት ከፍሎላቸዋል ይላል ጋዜጠኛው ኮልኒ።

ለኩባንያዎቹ ምን ተደርጎላቸው ነው መስዋዕት ተከፈለላቸው የሚባለው? ብዬ ጠየኩት። ምን መሰለህ ብሎ ንግግሩን ቀጠለ። እኔም ጆሮየን ቀጥ ቀጥ አድርጌ፣ ልቦናዬን ሰብስቤ፣ ዐይኔን ከፊቱ ተክዬ… ብእሬን ከማስታወሻዬ ጋር ለማሳሳም ቀስሬ ጠበኩት።

ኩባንያዎቹ ሲመሰረቱ በማለት ወጉን ቀጠለ። አገራችን የድሃ ድሃ ስለነበረች አብዛኛዎቹ ኩባንያዎች በዓለም አቀፍ ብድር ነው የተመሰረቱት። ዓለም አቀፍ ብድር ለማግኘትም ሌላው ፈተና ነበር። የወቅቱ የኮርያ መንግስት ፕሬዚዳንት ፓርክ ዋስትና በመስጠት ኩባንያዎቹ ከዓለም አቀፍ ባንኮች ብድር እንዲያገኙ ያግዙ ነበር። በመሆኑም በየተሰማሩበት የስራ ዘርፍ አምርተው በመሸጥ አትርፈው ብድራቸውን መመለስ ነበረባቸው።

ጀማሪ ኩባንያዎች በመሆናቸው ምርታቸው በጥራትም ሆነ በአቅርቦት ተወዳዳሪ ባለመሆናቸው በውጭ ኩባንያዎች ምርት ኪሳራ ውስጥ እንዳይገቡ የንግድ ከለላ ተደርጎላቸዋል።

በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1970 ዎቹ እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ ድረስ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ መንግስት ከፍተኛ ቁጥጥር ያደርግ ነበር አለኝ። ለአገር በቀል ኩባንያዎች ሲባል መንግስት ከውጭ አገራት ኩባንያዎች ማግኘት የነበረበትን የቀረጥ ገቢ ሊያጣ ችሏል።

የኮርያ ህዝብ ደግሞ የራሱ ኩባንያዎች የሚያመርታቸውን ምርቶች ቀድሞ በመግዛት ኩባንያዎቹ አቅም እንዲፈጥሩ መስዋዕትነት ከፍሏል። ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚገባው ህዝብ ለ30 ዓመታት ያህል በውድ ዋጋና ጥራቱ በዛው ልክ ያላደገ የኩባንያዎቹን ምርት በመጠቀም መስዋዕትነት ከፍሏል።

“እንደዛ በመሆኑም አሁን ላይ ከ80 በመቶ በላይ ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ ዶላር የሚያስገኙ በርካታ ኩባንያዎች ለማፍራት በቅተናል” በማለት የገለጸልኝን አስታወስኩ።

በማስታወስ ላይ እያለሁ የኛን አገር ሁኔታና ታሪካችን መመርመር ጀመርኩ። ስመረምር ግን ከኮርያዎች በተቃራኒ ሆኖ ሳገኘው ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ የተሰበሰበው ልቦናዬ ተበተነ፣ ቀጥ ብሎ የነበረው ጀሮየ ዛለ፣ አይኔ ቦዘዘ፣ ብእር የቀሰረው እጄ ራሴን ያዘ፣ አንገቴን ደፋሁ። ለምን ከእውነታና ከመርህ እየራቅን በተቃራኒ መጓዝ ቻልን? መንስኤውስ ምንድን ነበር? እንዴትስ ከዚህ መሰረታዊ ችግር መውጣት ይቻላል? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች በአእምሮዬ ተመላለሱብኝ።

ለመሆኑ ተሰጥኦ ያላቸውን ተንከባክቦ ወደሚፈለገው ደረጃ የማድረስ ባህሉም ሆነ እሴቱ አለን ወይ? ብዬ እራሴን ደግሜ ደጋግሜ ጠየኩ። ከጓደኞቼ ጋርም በዚህ ጉዳይ ማውራት ጀመርኩ ነገር ግን የመንከባከብ ባህል ያለን መሆኑን ማረጋገጥ አልቻልኩም። እንዳውም ተሰጥኦ ያለውን ሰው አንድም ከማህበረሰቡ ፈርጆ በማግለል አልያም ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የተሰራው ስራ የበዛ ሆኖ ታየኝ።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዶክተር አቢይ አህመድ በዓለም አደባባይ የኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው ባደረጉት ንገግር ብቻ በመማረክ ዓለም ለሁለት ደቂቃ ያክል ቆሞ ያጨበጨበላቸውን መሪ በአገራችን ከችግሮች ጋር እየተጋፈጡ መገኘታቸውን ያየ ምን ያህል ከእውነትና ከመርህ እንደራቅን መሆኑን በቀላሉ ማረጋገጥ ይችላል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ለመገመት በሚያዳግት መልኩ በርካታ ለውጦችን በሃገር አቀፍና በአጎራባች አገሮች እንዲመጣ አድርገዋል። እስረኞችን ፈትተዋል። የፖለቲካ ምህዳሩን ልቅ አድርገዋል። ማንኛውም ጋዜጠኛና ጸሃፊ የፈለገውን ሃሳብ የሚገልጹበት አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።

በአስከፊው ጦርነት ከሁለቱም አገራት ከ100 ሺህ በላይ ወታደሮችን ህይወት የቀጠፈው ጦርነትን ተከትሎ ከ20 ዓመታት በላይ በምሽግ ውስጥ ሆነው በፊት ለፊት ፍጥጫ የኖሩትን የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ወደ አልተጠበቀ ሰላም መልሰውታል።

ከሁሉም በላይ በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በመደመር… እሳቤዎቻቸው አዲስ የፖለቲካ አቅጣጫ ይዘው ብቅ ማለታቸው በአብዛኛው የአገራችን ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ አስችሎአቸዋል። ወደ ትልቁ ራዕያቸው ለመድረስ ትክክለኛውን መንገድ በፍቅር፣ በይቅርታና በመደመር እሳቤያቸው ጀምረውታል።

ዴሞክራሲን ለማስፋት የሚያስችሉ ተቋማትን መስረትዋል። የምንኖርባትን አገር ብዙና ህብረ ብሄራዊ ህዝብ በአንዲት ኢትዮጵያ በምትባል አገር መኖራችን፣ ስለ አገር ክብር፣ ልዕልናና ዝና የሚያደርጉት ወጥነት ያለው ንግግር አብዛኛውን ህዝብ በተስፋ እንዲሞላ አድርገዋል።

ወደ ታላቁ ራዕያቸው የኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግናን ማጎናጸፍ ለመድረስ ይቅርታ፣ ፍቅር፣ መተሳሰብና መደመር የአስፓልት መንገድ በመሆን ወደ ተፈለገው አቅጣጫ ለመውሰድ ጉዞው ተጀምሯል።

እርሳቸው ኢትዮጵያን ከነበረችበት የማጥ ፖለቲካ ለማውጣት ሲሯሯጡ የኛ ምላሽ ምን ነበር? የሚለውን ዋነኛው ጥያቄ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትራችን ደግፈን፣ ተንከባክበን፣ አግዘን ወደሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ሞክረናል? ወይስ በተቃራኒው ቁመናል? የሚለውን መመለስ አለብን ።

ዶክተር አቢይ በፍቅር፣ ይቅርታና መደመር እሳቤዎች በመንቀሳቀሳቸው ዛሬ ላይ ለዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚነት አብቅቷቸዋል። የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ዶላር፣ ሜዳሊያና ዲፕሎማ ተበርክቶላቸዋል።

በኬሚስትሪ፣ በስነጽሁፍ፣ በፊዝክስ፣ በህክምናና በሰላም አስተዋጽኦ ያደረጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከሚበረከተው ትልቁ የኖቤል ሽልማት ውስጥ የሰላም ኖቤልን ዶክተሩ መውሰዳቸው ለአፍሪካም ለኛም ኩራት ነው።

ዛሬ የዓለም ህዝብ ለኖቤል ሽልማት ያበቃቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር እኮ የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል አካባቢ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍና በተለያዩ አካባቢዎች ያልተሳካ የግድያ ሙከራ ተካሄዶባቸው እንደነበር የሚታወቅ ነው ።

ለዚህ ማሳያው በመስቀል አደባባይ  የፈነዳው ቦንብ አንዱ ሲሆን  ቡራዩ ጸጥታ ሲያስከብሩ የነበሩ የኮማንዶ ጦር ክፍሎች ቤተ መንግስት ድረስ እስከ ትጥቃቸው ለመግባባት የሞክሩበት ይጠቀሳል ። በእርሳቸው የአመራር ጥበብ ባይፈታ ኖሮ ጣጣው ምን ሊሆን እንደሚችል መገመቱ አይከብድም ።

ያመጡትን የፍቅር፣ የእርቅና የመደመር እሳቤያቸውን ደግፈንና እርሳቸውን ተንከባክበን በእሳቤያቸው ተጉዘን ራዕያቸው ወደ ሆነው ብልጽግና እድገት ማማ በሰላም እንደመውጣት በየመንገዳቸው ደንቃራ ሆነን መገኘታችን ከኮርያዎች በተቃራኒ ለመቆማችን ትልቅ ማሳያ ነው። ማሳያ ብቻ ሳይሆን መልካም ነገርን ተንከባክበን ወደሚፈለገው የተሻለ ደረጃ የማሳደግ ብቃታችን ችግር ያለበት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

አሁን በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ሽልማት አማካኝነት የዓለም ግዙፍ ሚዲያዎች በቀጥታ ስርጭት ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነት የተሰበከውን ንግግር ከምዕራብ እስከ ምስራቅ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ አስተጋብተዋል። እኔም ቀደም ሲል የደፋሁትን አንገቴን ቀና አድርጌ ከግድግዳው ከተለጠፈው ቴሌቪዥን አፍጥጬ ተመልክቻለሁ ። የተላለፈውን መልዕክትም አዳምጫለሁ። የዓለም ህዝብ ስለ ሃገራችን ያለው ምልክታ በአጭር ጊዜ ውስጥ መለወጡንም መገንዘብ ችያለሁ።

ጠቅላይ ሚኒስትራችን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ያመጡዋቸውን የለውጥ ችግኞች በተስማሚ ቦታ በመትከል፣ ኮትኩቶ፣ አርሞና ተንከባክቦ በማሳደግ፣ ፍሬ እንዲያፈራና ፍሬው ተለቅሞ ወይም ተመርቶ ለመላ ኢትየጵያውያን ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ የኛ የዜጎች ሚና ነው።

እኛም እንደ ኮርያዎች ለሁሉም የማይሰጠውን ተሰጥኦ ተንከባክበን ወደ ሚፈለገው ደረጃ የማድረስ ሃላፊነታችን ለመወጣት አሁን የተገኘው የኖቤል ሽልማት መልካም አጋጣሚና ወሳኝ መሆኑ ግልጽ ነው።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ እንዳሉትም “ይህ ታሪክ ለእኛ ኢትዮጵያውያን መልካም አጋጣሚ ነው።” ለመላ አፍሪካዊያንም ታላቅ ኩራት ነው በማለት ገልጸውታል።

መልካም አጋጣሚና ኩራት የሚሆነው ግን ያገኘውን ድል ጠብቀን መጓዝ ስንችል ብቻ ነው ይላሉ ዶክተር ፍሬው። አሁን ላይ የዓለም ሚዲያ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዙሯል። ከዚህ በኋላ መልካምም ሆነ መጥፎ ዜና ለማሰማት የዓለም ሚዲያ ከኢትዮጵያ መረጃ ማፈላለጉ አይቀርም።

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ በየአካባቢው ሰላም ለማስፈን ከልቡ መስራት ይጠበቅበታል። በአንዳንድ ክልሎች የሚከሰተው ሁከትና ብጥብጥ አሁን ላይ አድጎ የከፍተኛ ትምህርት ተቋት ውስጥ መሽጎ ይገኛል። ይህ ደግሞ ለዘመናት ተጭኖን ከኖረው የረሃብና የጦርነት ስዕል ጋር ተዳምሮ ለአገራችን ጥላሸት መሆኑ ግድ ነው። የግጭቱ መንስኤ ብሄር ተኮር በመሆኑ እልባት ለመስጠት አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ መላው የአገራችን ህዝቦች የችግሩን መንስኤ አውቀው ከሰሩ የማይፈታ ችግር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም።

ለዶክተር አቢይና ለሾሙዋቸው አመራሮች የየተሰጠው የሰላም ኖቤል ሽልማት ችግሩን ለመፍታት ታላቅ አቅምና ጉልበት ይፈጥርላቸዋል የሚል እምነት አለኝ። ለኢትዮጵያ ህዝብም ታላቅ ኩራት የሰነቀ በመሆኑ አሁን የሚስተዋሉ ሳንካዎችን በማስወገድ ዓለም ወደ ሚጠብቀን የብልጽግናና የእድገት ማማ ለመጓዝ መንቀሳቀስ አለብን ብለዋል። ሽልማቱ “ታላቅ ነበርን ታለቅም እንሆናለን!” የሚለውን መርህ እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው ።

ይህ ካልሆነ ግን የኖቬል ሽልማቱ የአንድ ሰሞን ዜና ሆኖ መቅረቱ አይቀርም። ይህን በመገንዘብም በየአካባቢው የሚስተዋሉ ሳንካዎችን በጋራ ለማስወገድ መረባረብ ግድ ይልናል።

በተገኘው ድል ታግዘን ችግሮችን በውይይትና በድርድር በመፍታት ወደ ታላቅነት የምናደርገውን ጉዞ ማፋጠን የአሁኑ ትውልድ ድርሻ ነው።

ይህን ማድረግ ከቻልን ተሰጥኦ ያላቸውን … ደግፎና ተንከባክቦ ወደ ትልቅ ደረጃ የማድረስ ባህል አጎለበትን ማለት ነው። የኛን ድጋፍ ከታከለበት ገና ከጅምሩ ጎልቶ የወጣው መሪ ገና አሸብርቆ ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም