አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር ተወያዩ

ኢዜአ ታህሳስ 03 / 2012 ዓ.ም በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ከሱዳን ሪፐብሊክ የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር ትናንት ተወያይተዋል። አምባሳደር ሽፈራው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብዳላ ሐምዶክ ጋር በወቅታዊ የኢትዮጵያውያን የኑሮ ሁኔታ እና የሁለትሽ ግንኙነት ዙሪያ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጸህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካካል ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር ብሎም በወደብ አጠቃቀም፣ በመንገድ፣ በባቡር እና በተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለመተሳሰር፣ የኢኮኖሚ ስቲሪንግ ኮሚቴ ስብሰባን ለማካሄድ በሚከናወኑ የዝግጅት ተግባራት ዙሪያ እንዲሁም በሌሎች የሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል።

አምባሳደር ሽፈራው በቅርቡ የሱዳን መንግስት ያወጣውን የውጭ ዜጎች በተለያዩ የንግድ ስራዎች እንዳይሰማሩ የሚያግደውን ሕግ አፈጻጸም ተከትሎ አፈሳና እስርን ጨምሮ በዜጎች ላይ የተለያዩ እንግልቶች እየደረሱባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

መታወቂያ እና የመኖሪያ ፈቃድ ባላቸው ዜጎች ላይ ጭምር የሚጣለው ከ50ሺ እስከ 100ሺ ጁኔህ (የሱዳን መገበያያ ገንዘብ) የሚደርስ የተጋነነ ቅጣትና በፍርድ ቤቶች አካባቢ ያለተገቢ ማጣራት በቅጽበት የሚሰጡ ፍርዶችን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ለሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ማሳወቃቸውን በማውሳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትኩረት እንዲያዩት እና እልባት እንዲሰጡት ጠይቀዋል፡፡

የሱዳን መንግስት መንግስት በኢትዮጵያና ሱዳን መካካል ያለውን የወንድማማች ግንኙነት እንዲሁም ለዘመናት የዘለቀ ታሪካዊ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ከግምት ውስጥ እንዲያስገባም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብደላ ሐምዶክ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካካል ያለውን ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አውስተዋል።

በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለአገሪቱ ኦኮኖሚ ጉልህ አበርክቶ ያላቸው መሆኑን በመጥቀስ በቅርቡ የወጣው ሕግ ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ጋር በመነጋጋር አፈሳው እንዲቆም እና በፍርድ ቤቶችና በጸጥታ አካላት የሚደርሱ ጥፋቶችን አስመልክቶ ሪፖርት እንዲቀርብላቸው መመሪያ ማስተላለፋቸውን ጠቅሰው ለጉዳዩ በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት እንደሚያገኝ ማረጋጋጫ ሰጥተዋል።

በውይይቱ ወቅት አምባሳደር ሽፈራው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የላኩላቸውን መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም