በሰላም እሴት ግንባታ ውስጥ የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል – አቶ ከበደ ጫኔ

3185

ሰኔ15/2010 በሀገሪቱ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማት በሰላም እሴት ግንባታ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አሳሰበ።

በሀገሪቱ የሰላም እሴት ግንባታና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ውስጥ የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።

የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና ዘላቂ ልማት የሚረጋገጠው የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማት በሰላም እሴት ግንባታ የማይተካ ሚና መጫወት ሲችሉ ነው፡፡

በሀገሪቱ የተገነባውን ህብረ ብሔራዊ ፌዴራልዝም ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማት ሚናቸውን መጫወት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የመድረኩ ዓላማም ሚዲያዎች በሰላም እሴት ግንባታ ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና ይበልጥ ለማጠናከርና የሚዲያ አካላት የሰላም ፎረም ለማደራጀት መሆኑን ገልጠዋል።

”ግጭቶችን በመከላከል፣ አስተማማኝ ሰላም በማስፈንና ዜጎች ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ባለቤት እንዲሆኑ የሚዲያው ዘርፍ ሊወጣ በሚገባው ኃላፊነት ላይ ለመምክር ጭምር ነው” ብለዋል።

”የሚዲያ ተልዕኮ በሀገራዊ ፖሊስና ስትራቴጅ ላይ ህብረተሰቡ ግልጽ ግንዛቤና እውቀት እንዲኖረው ማድረግ ነው” ያሉት አቶ ከበደ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ደግሞ ህዝቡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ  ተሳትፎ እንዲጠናከር ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የመንግስት ኃላፊዎች እለት ተእለት የሚያከናውኑትን ሥራዎች ለህበረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ አለባቸው ያሉት ሚኒስትሩ የሰላም ባህል ሊገነባ የሚችለው በሰው አእምሮ ውስጥ በመሆኑ የሰዎችን አመለካከት፣ግንዛቤና አስተሳሳብ ለመለወጥ በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።

የሚዲያ ባለሙያዎችና ተቋማት በህዝቦች መካከል ጥርጣሬና ጥላቻ ከሚፈጥሩ ድርጊቶች በመቆጠብ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጠናከር፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲገነባ፣ ፈጣንና ፍትሃዊ ልማት እንዲረጋገጥ ሌት ተቀን ህዝቡን የማስተማርና የማሳወቅ ሥራ መስራት እንደሚገባቸው አስገዝበዋል።

የሚዲያ ተቋማት የተጫወቱት አውንታዊ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ ሀገራዊ የሰላም እሴቶችን ከማጎልበት፣ ብሔራዊ መግባባትና አንድነት እንዲጠናከር ከመስራት ይልቅ መራራቅና መቃቃር ይበልጥ በህዝቦች መካከል እንዲሰፋ የሚሰብኩ አንዳንድ ሚዲያዎች እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡

የሰላም እጦት ዋነኛ መነሻው ኢፍትሃዊ የሆኑ አሰራሮች፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የፖለቲካ ተሳትፎ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሚኒስትሩ የሰላም እሴት ግንባታና አስተምህሮ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አቶ ሰይድ መንዲስ ናቸው።

በመድርኩ ላይ ባቀረቡት ጹሕፍ እንደገለጹት አሁን የታየውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ከራሳችን ጀምረን ስለ ሰላም መዘመር አለብን ብለዋል።

ሚዲያው በዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ እኩልነትና ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ መስራት እንደሚገባው አመልክተዋል።

በአዳማ ከተማ ለአንድ ቀን በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ከፌዴራልና ከክልል የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።