በስፖርታዊ ጨዋነት አርአያ እንደሚሆኑ የደጋፊ ማህበራት ገለጹ

71
ኢዘአ ታህሳስ 03/2012 የተጋጣሚ አቻዎቻቸውን በስፖርታዊ ጨዋነት አስተናግደው በፕሪሜየር ሊግ የውድድር ዓመቱ አርአያ እንደሚሆኑ በትግራይ የክለቦች ደጋፊዎች ማሀበራት ገለጹ። የወልዋሎ ደጋፊዎች ማህበር የቦርድ አባል አቶ ገብረገርግስ ሓዱሽ “ በፕሪሜር ሊግ የእግር ኳስ ውድድሮች ስፖርታዊ ጨዋነት በሚያጎድሉ ደጋፊዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን “ብለዋል። ውድድሩ ሰላማዊና ጥሩ ፍክክር የሚታይበት ስፖርት እንዲሆን ችሎም የአባላቱና ስፖርት አፍቃሪው ክብር ለመጠበቅ ማህበሩ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ጥሩ ለተጫዋተ ክለብ ስፖርታዊ ድጋፍ በመለገስ፣ የተጫወቾች ክብርና ሞራላቸው በመጠበቅ ስፖርት የሰላም፣ የፍቅርና አንድነት መገለጫ እንዲሆን አበክረው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል። የመቀሌ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ማህበር ምክትል ፕረዘዳንት አቶ ይርጋ ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው የአንድ ክለብ ደጋፊዎች ስራ ለተጋጣሚው ፍቅርና ክብር በማሳየት ስፖርት የአንድነትና የፍቅር ማገለጫ መሆኑን ማሳየት እንደሆነ ተናግረዋል። “ከዚሁ ውጭ ተመልካችንም ሆነ ተጫዋች በመዝለፍና የክለቡ ስም በማጉደፍ ስፖርቱ የሚያውኩን በማጋለጥ ስፖርታዊ ጨዋነት የተላበሰ እንዲሆን እንሰራለን “ ብለዋል። ባለፈው ዓመት በሀገሪቱ የታየው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል  እንዳይደገም በራሳቸውም ይሁን በተጋጣሚዎቻችን ሜዳ ስፖርቱ በሰላማዊ መንገድ ማካሄድ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ደጋፊዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አረዓዶም በሪሁ ናቸው። የመቀሌ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ማሀበር አባል ወጣት ንጉስ ኪዳነ  “ሁከት ለመፍጠር በሚሞክሩ ተመልካቾችና ደጋፊዎች ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ተገቢውን ተግሳፅና ቅጣት እንዲያገኙ በትብብር እንሰራለን “ ብሏል። የፕሪሜር ሊግ ውድድሮች ስፖርታዊ ጨዋነትና ጤናማ ውድድር ሆኖ እንዲጠናቀቅ በአርአያነት  እንደሚሰሩ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል። የትግራይ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና ፀሃፊ አቶ አንገሶም ካሕሳይ እንዳሉት የደጋፊዎቸ ማህበራት ተባብረውና ተደራጅተው በእግር ኳስ ዙሪያ የሚታየውን የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ለማስተካከል የላቀ ሚና አላቸው። ውድድሩ ሰላማዊና ስፖርት አፍቃሪውም በጨዋታው ረክቶ እንዲወጣ ማህበራቱ የጀመሩት በጎ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እንደሚሰጥም ተመልክቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም